Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር የ67 አውሮፕላኖች የግዢ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 4 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የአቪዬሽን ታሪክ ትልቁ የተባለለትን 67 ቦይንግ ጀት አውሮፕላኖች የግዢ ሥምምነት ተፈራረመ፡፡

በሥምምነቱ መሰረት አየር መንገዱ 11 ቦይንግ 787 ድሪምላይነር እንዲሁም 20 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ይገዛል።

ከዚህ ባለፈም 15 ቦይንግ 787 ድሪም ላይነር እና 21 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን በተጨማሪነት የመግዛት አማራጭን ያካተተ ሥምምነት መሆኑን አየር መንገዱ አስታውቋል።

የግዢ ሥምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እና የቦይንግ ኩባንያ የንግድ ግብይት እና ሽያጭ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ብራድ ማክሙለን ተፈራርመውታል።

አሁን የታዘዙት አውሮፕላኖች የነዳጅ ፍጆታን በመቀነስና የከባቢ አየር ብክለትን በመቀነስ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል መባሉን መረጃው ያመላክታል።

ከዚህ ባለፈም አየር መንገዱ የደንበኞቹን ምቾት እና ፍላጎት በመጠበቅ ተመራጭነቱን ለማሳደግና ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚያግዘውም በፊርማ ሥነ ሥርአቱ ወቅት ተገልጿል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በቦይንግ መካከል ለአመታት የቆየውን የንግድ አጋርነት ያጠናክራል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም÷ የአየር መንገዱን የበረራ አገልግሎት የበለጠ ለማጠናከር እና ለማስፋፋት እንደሚስችል ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.