ቢዝነስ

ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ወራት 64 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ሰበሰበ

By Alemayehu Geremew

November 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት አራት ወራት 64 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 95 በመቶ ማሳካቱን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በአራት ወራት የተከናወኑ ሥራዎችን የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል፡፡

በገቢ አሰባሰብ፣ ኮንትሮባንድ እና ሕገ- ወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ናቸው መባሉን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ÷ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ወራትም በበጀት ዓመቱ የተያዘውን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡