አፈ-ጉባዔ አገኘሁ በቻይና የብሔራዊ ሕዝብ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በኢትዮጵያ ከሚገኙት በቻይና የብሔራዊው ሕዝብ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ሎሳንግ ጊልትሰንና ልዑካን ቡድናቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡
በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው ግንኙነት በፈረንጆቹ ከ1970 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በጠነከረ ወዳጅነትና አጋርነት መዝለቁ ታሪካዊ ነው ተብሏል፡፡
ሀገራቱ ያላቸው ግንኙነት ከፍ ወዳለ የመንግሥታት ግንኙነትና አጋርነት መለወጡም ትልቅ ማሳያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከቻይና መንግስት የወሰዳቸው ጠቃሚ ልምዶች እንዳሉ አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡
ለተማሪዎች ምገባ፣ ለወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለወጣት ተማሪዎች እየተሰጠ የሚገኘው ነጻ የትምህርት ዕድል ኢትዮጵያን የእውቀት ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ለእድገቷም ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ምክትል ሊቀመንበር ሎሳንግ ጊልትሰ በበኩላቸው÷ የኢትዮ ቻይና ግንኙነትና አጋርነት ቆየት ያለ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ቻይናውያን በኢትዮጵያ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ መሰማራታቸው የሀገራቱ ግንኙነት ነባር ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው መሆኑን አስረጂ ከመሆኑም ባሻገር ሀገሪቷ ለውጪ ባለሀብቶችና ለኢንቨስትመንቶች ምቹ ስለመሆኗ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሽብርተኝነት ለመከላከል ያለውን ጽኑ ፍላጎትና ተነሳሽነት መንግስታቸው እንደሚደግፍም አስረድተዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ የንግድ፣ የባህል፣ የማህበራዊ፣ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ግንኙነቶች አሉ ተብሏል፡፡
ግንኙነቶቹን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ሁለቱ ሀገራት ተቀራርበው በመስራት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሚስተዋሉ የሰላም ችግሮችን እልባት ለመስጠት ከስምምነት ላይ መደረሱም ተገልጿል፡፡
የልኡካን ቡድኑ በቀጣይ ቀናትም ከተለያዩ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚወያይ የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡