የልጆችን በሽታ የመከላከል አቅም እንዴት መጨመር ይቻላል?
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህጻናት በቀላሉ እንዳይታመሙ በሽታ የመከላከል አቅማቸው መጎልበት አለበት፡፡
ይህንንም ለማድረግ መሠረታዊ መርሆችን መከተል ይገባል፡፡
እነሱም፡-
-ጡት ማጥባት፡- ቢያንስ ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ጡት ብቻ ማጥባት የራሱ የሆኑ ጠቀሜታዎችን የሚሰጥ ሲሆን÷ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጡት ማጥባት አለርጂ የመያዝ እድልን ይቀንሳል፡፡
– በየጊዜው እጅ መታጠብ፡- ልጆችን ሲያስነጥሱ፣ ሲያስሉ እና ወደ መጸዳጃ ቤት ከሄዱ በኋላ እጃቸውን ለመታጠብ ጊዜ እንዲወስዱ አስተምሯቸው።
– እጅን በሞቀ ውሃ እና ሳሙና ቢያንስ ለ20 ሰከንድ መታጠብ ባክቴሪያዎችን እና ቫይረሶችን ያስወግዳል፣ እስከ 45 በመቶ የሚደርስ የሳንባ ኢንፌክሽን እድልንም ይቀንሳል።
– የክትባት ወቅትን አለማሳለፍ፡- በልጅነት የሚወሰዱ ክትባቶች እንደ ኩፍኝ ፣ ጉድፍ፣ ፖሊዮ እና ሮታ ቫይረስን ስለሚከላከል የክትባት ጊዜ ፈጽሞ አያምልጣቸው፡፡
– አመጋገብን ማስተካል፡- ትክክለኛ የምግብ ምርጫ ልጅዎ በቂ ቫይታሚኖችን ማግኘቱን ለማረጋገጥ ይረዳል፤ ጤናን ለመጠበቅ እና ጠንካራ የበሽታ መከላከል ስርዓትን ለመጠበቅ ቫይታሚኖች ያስፈልጋሉ።
– በቂ እንቅልፍ ማግኘት፡- ልጆች በሽታ የመከላከል አቅማቸው ከፍ እንዲል በቂ እንቅልፍ ማግኘት ያለባቸው ሲሆን የእንቅልፍ ሰአቱ እንደ እድሜያቸው መጠን ይለያያል፡፡
በዚህም ከ0 እስከ 3 ወር ያሉ ህጻናት ከ14 እስከ 17 ሰአታት መተኛት ያስፈልጋቸዋል፤ ከ 4 እስከ 12 ወራት ውስጥ ያሉት ከ 12 እስከ 16 ሰአታት መተኛት ያስፈልጋቸዋል::
ከ 1 እስከ 2 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ደግሞ ከ11 እስከ 14 ሰዓታት መተኛት ያስፈልጋቸዋል፤ ከ 3 እስከ 5 ዓመት እድሜ ያላቸው ልጆች ከ 10 እስከ 13 ሰአታት እንቅልፍ ማግኘት እንዳለባቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡