የኢትዮጵያ የባህር በር የጋራ ተጠቃሚነት ጥያቄ አማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው – ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር የጋራ ተጠቃሚነት ጥያቄ አማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለጹ።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ አስመልክቶ ከፋና ብሮድካስቲንግ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የኤርትራ ነጻነት ከመታወጁ በፊት በተካሄደው የቻርተር ጉባኤ ላይ መሳተፋቸውን ያስታወሱት ፕ/ር በየነ፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ጥያቄ ሲነሳበት እንደነበር ጠቅሰዋል።
ኤርትራ በሪፈረንደም ነጻ ስለመውጣት ወስናለች ተብሎ በቻርተር ጉባኤ አቅጣጫ ሲቀመጥ የባህር በሩስ እንዴት ነው ስምምነት ላይ የሚደረሰው የሚል ጥያቄ በወቅቱ ተነስቶ ነበር ብለዋል።
ለተነሳው ጥያቄ ከኤርትራ ፖለቲካ መሪዎች ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል የሚል ምላሽ ተሰጥቶበት እንደነበር አስታውሰዋል።
በወቅቱ ታዲያ በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል የባህር በር የጋራ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ስጋቶችና የሚነሱ ጥያቄዎች ነበሩ ብለዋል ፕሮፌሰር በየነ።
ለዘመናት የኢትዮጵያ መሆኑ የሚታወቀው የባህር በር ከኢትዮጵያ እጅ ወጣ ማለት የህዝባችንን ጉሮሮ የሚያንቅ ነው፤ ስለዚህ ይህንን ነገር መፍቀድ ማለት በታሪክ ያስጠይቀናል እስከማለት ተደርሷል ሲሉ ገልጸዋል።
በፖለቲካ መሪዎቹ ዘንድ ወደቦቹን በጋራ እንጠቀማለን የሚል ቃል ከመገባቱ ባለፈ በጽሁፍ የተገባ ውል ስለመኖሩም ተጠይቆ እንደነበር አንስተዋል።
ያ ሁሉ ሆኖ በጊዜ ሂደት የሁለት ወደብ ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ከወደብ ተጠቃሚነት ተነፍጋ ቆይታለች።
በመሆኑም የባህር በር ጥያቄው መነሳቱ ተገቢነት ያለው ነው ያሉት ፕ/ር በየነ፤ የጋራ ተጠቃሚነት ጥያቄው አማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው በማለት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄውን መቼም ቢሆን መጠየቅ አለባት፤ መደራደር እፈልጋለሁ ማለት አለባት ሲሉም ገልጸዋል።
ጥያቄው ውጤት እንዲያመጣ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ምሁራንን ጨምሮ የሚመለከታቸውን ለውይይት መጋበዝ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
የጉዳዮችን ምክንያታዊነት በግልጽ በማስቀመጥ የጎረቤት ሀገራትን ምሁራንና ህዝብን ያሳተፈ ስራ በመስራት ማሳመን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በሳሙኤል ወርቅአየሁ