የኮሌራ በሽታ ምልክቶች እና በሽታው ሲታይ መከናወን ያለባቸው ተግባራት
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሌራ በሽታ በአይን በማይታ ረቂቅ ተህዋስያን አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው።
በሽታው በአስቸኳይ ህክምና ካላገኘ ለሞት የሚዳርግ መሆኑም ይነገራል፡፡
የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶችም መጠኑ የበዛ የሩዝ ውሃ የሚመስል አጣዳፊ ተቅማጥ፣ ትውከትና የአፍ አካባቢ መድረቅ ይገኝበታል፡፡
የኮሌራ በሽታ መተላለፊያ መንገዶች፦ በበሽታው በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው በከፍተኛ ፍጥነት ይተላለፋል፣ ንፁህ ባልሆኑ እጆች ምግብን በማዘጋጀት፣ በማቅረብና በመመገብ፣ በሽታ አምጪ ተህዋስያን የተበከለ የምንጭ፣ የጉድጓድ፣ የወንዝ፣ የዝናብ፣ ቧንቧ ወዘተ ውሃን መጠቀም፡፡
በሽታ አምጪ ተዋህስያን የተበከለ የውሃ ማጠራቀሚያ እና መገልገያ እቃዎችን መጠቀም፣ ክዳን የሌላቸውን እና ለዝንብ የተጋለጡ የምግብ ማስቀመጫ እና መመገቢያ እቃዎችን መጠቀም፣ በሽታ አምጪ ተዋህስያን የተበከሉ ምግቦችን፣ አትክልቶችና ፍራፍሬዎችን በመመገብ እንዲሁም መፀዳጃ ቤቶችን በአግባቡ ባለመጠቀም ይተላለፋል።
መከላክያ መንገዶቹ፦ ሁልጊዜ ውሃ አፍልቶ በማቀዝቀዝ ወይም በውሃ ማከሚያ ኬሚካል የታከመ ውሃ መጠቀም፣ ምግብን በሚገባ አብስሎ በትኩሱ መመገብ፣ የምግብ እቃዎችን በንጹህ ወይም በኬሚካል በታከመ ውሃ ማጠብ እና መጠቀም፣ መጸዳጃ ቤትን አዘጋጅቶ በአግባቡ መጠቀም ይገኝበታል፡፡
እንዲሁም እጅን ከመጸዳጃ ቤት መልስ፣ ምግብ ከማዘጋጀት በፊት፣ ምግብ ከማቅረብዎ በፊት፣ ምግብ ከመመገብዎ በፊት፣ ሕጻናትን ካጸዳዱ በኋላ፣ ሕጻናትን ጡት ከማጥባትዎ በፊት፣ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች እንክብካቤ ካደረጉ በኋላ፣ በበሽታው የሞቱ ሰዎችን አስክሬን በድንገት ከነካኩም በሳሙና እና ሳሙና ከሌለ በአመድ በሚገባ መታጠብ ይመከራል፡፡
ማንኛውንም ከቤት የሚወጣ ደረቅ ወይም ፈሳሽ ቆሻሻ ውሃ እና አካባቢን እንዳይበክል በአግባቡ በተመደበለት ስፍራ ማስወገድ፣ በኮሌራ በሽታ የታመመን ሰው ልብስ በፈላ ውሃ መቀቀል ወይም በበረኪና በልብስ ማጽጃ ሳሙና ዘፍዝፎ ማጠብ፣ የኮሌራ መከላከያ ከትባት መከተብ፣ የበሽታው ምልክት የታየበትን ሰው በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም በመውሰድ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ ማድረግም ሌላው የኮሌራ በሽታ መከላከያ መንገድ ነው፡፡
የኮሌራ በሽታ ምልክት ሲታይ በሽታው ፈሳሽ እና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን በብዛት ከሰውነት የሚያስወጣ ስለሆነ የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ይገባል፡፡
እነሱም በመጀመሪያ በቤት ውስጥ ማንኛውንም ንፅህናው የተጠበቀ ፈሳሽ መውሰድ፣ ሕይወት አድን ንጥረ ነገሮች ወይም ኦ አር ኤስ በቤት ውስጥ ካለ ፈልቶ በቀዘቀዘ በአንድ ሊትር ውሃ በመበጥበጥ መጠጣት የተበጠበጠ ኦ አር ኤስ መጠጣት የሚቻለው በተበጠበጠ በ24 ሰዓት ውስጥ ነው፡፡
ኦ አር ኤስ በቤት ውስጥ ከሌለ 6 የሻይ ማንኪያ ስኳር እና ግማሽ የሻይ ማንኪያ ጨው በአንድ ሊትር ንጹህ ውሃ በመበጥበጥ መጠጣት እንደሚገባ ከአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ጡት የሚጠቡ ህፃናት በበሽታው ከተጠቁ ጡት ማጥባቱን ከወትሮው በበለጠ መጨመር እንዲሁም በአስቸኳይ አቅራቢያዎ ወደሚገኝ የህክምና ተቋም በመሔድ ህክምና እንዲወስዱ ማድረግ።