Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት አድርገዋል – እዮብ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 10 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ”ጂ-20 ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ” ጉባዔ አስቀድሞ ከጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች በጋራ ትብብር መስኮች፣ በሀገር ውስጥና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

ውይይቱን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፥ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለበርካታ ዓመታት የቆየና ጠንካራ መሆኑን ገልፀዋል።

የጀርመን መንግሥት በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍን ለማጠናከር እንዲሁም ሀገሪቱ የምግብ ዋስትና እንድታረጋግጥ ትብብር እያደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ግንኙነት በአዳዲስ የትብብር መስኮች ለማጠናከር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንን ተከትሎም በተለይም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመደገፍ እንዲሁም በአረንጓዴ ልማት የኢንቨስትመንትና የልማት ትብብር ለማድረግ መወያየታቸውንም ነው የተናገሩት።

ይህም ብቻ ሳይሆን በግብርናው ዘርፍ ያለውን አጋርነት ለማጠናከር እንዲሁም የባለብዙ ወገን ዘርፍ አጋርነትን ለማጎልበት ሁለቱ መሪዎች መግባባት ላይ ደርሰዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.