Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ከነገ ጀምሮ የችግኝ እንክብካቤ ይከናወናል

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ክረምት የተተከሉ ችግኞችን በዘመቻ የመንከባከብ ስራ ከነገ ህዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚከናወን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ÷በክልሉ ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በስፋት ሲካሄድ መቆየቱን ጠቅሰው ባለፈው ክረምትም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።

ዘንድሮ የተተከሉ ችግኞች ለፍሬ እንዲበቁ ከነገ ጀምሮ የችግኝ እንክብካቤ ዘመቻ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በመኸር አዝመራ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር በስንዴ የለማ ሲሆን÷ 85 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በ314 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ ተዘርቶ ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሩዝ ልማትም በክልሉ በስፋት መከናወኑን ጠቅሰው በክልሉ በመኸር የለማው ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ አርሶ አደሩ ያለውን አቅም ሁሉ በምርት ስብሰባው ላይ ማዋል እንዳለበትም አሳስበዋል።

በኦሮሚያ ክልል 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ስራ የተጀመረ ሲሆን÷ እስካሁን በተሰራው ስራም 863 ሺህ ሄክታር በዘር መሸፈኑን ነው የተናገሩት።

ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱም ከ100 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይገኛል ተበሎ እንደሚጠበቅም ሃላፊው ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.