Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሄ ያገኙ ዘንድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች- አቶ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሄ ያገኙ ዘንድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እንደምታደርግ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፡፡

የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላትና ቋሚ ኮሚቴዎች አዲስ አበባ ላይ የጋራ ስብሰባቸውን እያካሄዱ ነው፡፡

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በጉባኤው ላይ ባደረጉት መክፈቻ ንግግር÷ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት መመስረት የነበራት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይም የሚስተዋሉት ችግሮች ተቀርፈው የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የጸና አቋም አላት ብለዋል፡፡

የፓርላማ ዲፕሎማሲ የጋራ ችግሮቻችንን ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው÷የፓን አፍሪካ ፓርላማም የቁልፍ ችግሮች መፍቻ በመሆኑ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

አፍሪካ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት እንዲሁም ከፍተኛ የመልማት አቅም ያላት በመሆኗ በአህጉሪቱ እየተስተዋለ ላለው ችግር መፍሄ ማምጣት ከተቻለ የአፍሪካን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በአፍሪካ አህጉር እየተስተዋሉ ካሉት ችግሮች መካከል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ድህነት እና የእርስ በርስ ግጭት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አፈ-ጉባኤው ጠቅሰዋል፡፡

ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በትብብር ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የፓን አፍሪካ ፓርላማ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አሸብር ወ/ጊዮርጊስ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷በአፍሪካ እየተባባሰ የመጣው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.