Fana: At a Speed of Life!

ሙሉዓለም የባህል ማዕከል በ7ኛው የዓለም የባህልና ሙዚቃ ፌስቲቫል ሊሳተፍ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሙሉዓለም የባህል ማዕከል በህንድ ሀገር በሚካሄደው 7ኛው የዓለም የባህልና ሙዚቃ ፌስቲቫል ኢትዮጵያን ወክሎ እንደሚሳተፍ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልሉ ሙሉዓለም የባህል ማዕከል 16 የሚደርሱ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞችን ይዞ ከህዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለ12 ቀናት ያህል ለአራት የህንድ ከተሞች የኢትዮጵያን ባህል፣ ኪነ-ጥበብና እሴቶች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማኻዲ እንደገለጹት፥ በመድረኩ የሀገራችንን ባህልና ኪነ ጥበብ የማስተዋወቅና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሚመጡ የባህልና ኪነ ጥበብ ልዑካን ጋር የልምድ ልውውጥ ይደረጋል።

ዓለም አቀፍ መድረኩ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሀገራት ጋር በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የልዑክ ቡድኑ መሪ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ከክልሉ የባህል ሙዚቃዎችና ውዝዋዜዎች በተጨማሪ የኢትዮጵያን ብሔር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ሙዚቃዎችና ውዝዋዜዎች ላይ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ማዕከሉ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ ያለው በመሆኑ ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እንደሚወጣ አልጠራጠርም ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.