Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ብቻ 88 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ የ4 ሺህ 48 የላብራቶሪ ምርመራ 88 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዚህም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 582 መድረሱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ ባወጡት ሪፖርት አስታውቀዋል።

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ እድሜያቸው ከ8 እስከ 75 ዓመት የሆኑ 51 ወንዶችና 37 ሴት ናቸው።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 55 ሰዎች ደግሞ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ 13 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው እንምዲሁም 20 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 73 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፥ ከእነዚህም መካከል 50 ሰዎች የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ 19 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም 1 ሰው ደግሞ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ናቸው።

8 ሰዎች ከትግራይ ክልል (ሁሉም የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው)፣ 4 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል (2 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው እና 2 ሰዎች ደግሞ የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው፤ ነዋሪነታቸው አምቦ፣ ቡራዩ፣ ሰንዳፋ እና ሞጀኖ ከተሞች)፣ 1 ሰው በሀረሪ ክልል ክልል (በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላት) እንዲሁም 2 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸውና የድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪዎች መሆናቸውን ዶክተር ሊያ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በትናንትናው እለት 1 ሰው ከኦሮሚያ ክልል ቫይረሱ ያገገመ ሲሆን፥ በአጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 152 መድረሱንም አስታውቀዋል።

በ24 ሰዓታት ውስጥ የተደረጉ የላቦራቶሪ ምርመራ ናሙናዎቹ ከተለያዩ ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ተወድስ የተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ81 ሺህ 10 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 582 ደርሷል።

አሁን ላይ 423 ሰዎች በህክምና ላይ ሲሆኑ፥ እስካሁንም 152 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል፤ የ5 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 2 ሰዎች ወደ ሀገራቸው ጃፓን መመለሳቸው ይታወሳል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.