የዓይን የሞራ ግርዶሽ መንስዔዎችና ህክምናው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዕይታ ከሚረዱ የዓይን ክፍሎች ውስጥ ሌንስ የሚባለው ክፍል ግርዶሽ ሲያጋጥመው የዓይን የሞራ ግርዶሽ ይባላል፡፡
የዓይን ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ሻምበል ኢንዶሎ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ፥ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት ዝቅተኛ የእይታ መጠንን እንዲሁም የዓይነ ስውርነትን እያስከተለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዋናዎቹ መንስዔዎች ብለው ያነሷቸውም ፥ ዕድሜ፣ የዓይን ምት(አደጋ፣ )ሲጋራ ማጨስ፣ ከፍተኛ የአልኮል መጠን መውሰድ፣ የስኳር እና የደም ግፊት ህመም የሚጠቀሱ ሲሆን ፥ አልፎ አልፎ በዘር ሊመጣ እንደሚችልም ነው የገለጹት፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ 20 ሚሊየን የሚሆን የዓለም ህዝብ በዓይን ሞራ ግርዶሽ አማካኝነት የዓይን እይታቸውን ማጣታቸውን ገልጿል፡፡
ይህም ማለት የዓይነ ስውርነትን ከሚያስከትሉ የዓይን እክሎች 51 በመቶውን የሚሸፍን እንደሆነ በጥናት መረጋገጡን ነው የተናገሩት፡፡
90 በመቶ የሚሆነው ዓይነ ስውርነት በታዳጊ ሀገራት እንደሚከሰትም ዶክተር ሻምበል ኢንዶሎ አንስተዋል፡፡
መከላከያ መንገዶቹም ሲጋራ አለማጨስ፣ የአልኮል መጠጥን መቀነስ ወይም አለመውሰድ፣ ከአጋላጭ አደጋዎች ራስን መጠበቅ እንዲሁም ተያያዥ ችግሮችን ማስወገድ ይገኙበታል፡፡
ህክምናውም፡- የሞራ የእድገት መጠን የሚቀንስ መድኃኒት እስካሁን ባለመገኘቱ ቀዶ ጥገናአማራጭ ህክምና እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም ማንኛውም የዓይን ችግር ሲኖር ቀደም ብሎ ሀኪም ማማከረና ህክምና ማድረግ ከሞራ ግርዶሽም ሆነ ከሌሎች የዓይን እክሎች የዓይነ ስውርነት እንዳያስከትሉ ይረዳልም ነው ያሉት የዓይን ህክምና ስፔሻሊስቱ ፡፡
በተለይም 40 እና ከ40 በላይ የሆናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የዓይን ምርመራ ቢያደርጉ ሲሉም የህክምና ባለሙያው ይመክራሉ፡፡
የሚመለከተው አካልም ለዓይን ሞራ ግርዶሽ ጤና እና ህክምና ትኩረት ሰጥቶ የቀዶ ህክምና የሚደረግበትን አቅም ማሳደግ እንዲቻል እገዛ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡