ሙስና የምሬት ምክንያትና የሀገር የእድገት ጸር በመሆኑ በጋራ መታገል ይገባል – አቶ ተስፋዬ ዳባ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልሹ አሰራርና ሙስና የምሬት ምክንያትና የሀገር የእድገት ጸር በመሆናቸው በጋራ መታገል ይገባል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ ገለጹ።
በጸረ-ሙስና ትግሉ መንግስት ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም አስታውሰዋል።
20ኛውን ዓለም አቀፍ የሙስና ቀን በማስመልከት “ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው፤ በሕብረት እንታገል” በሚል መሪ ሃሳብ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት የምክክር መድረክ እያካሄዱ ይገኛሉ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ÷ ኢትዮጵያ በምታደርገው የእድገትና ብልጽግና ጉዞ ላይ ሙስና እንቅፋት እየፈጠረ ያለ ከፍተኛ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የብልሹ አሰራርና የሙስና ችግሮች የዜጎች የምሬት ምክንያትና የሀገር የእድገት ጸር መሆኑን ገልጸው፤ በሀገር እድገትና ብልጽግና ላይ ከፍተኛ እንቅፋት የሆነውን ሙስና በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።
ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል እያደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪ የዜጎች እገዛ ወሳኝ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጸረ-ሙስና ትግሉ መንግስት ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይነት የተጠናከሩ ስራዎችን የሚያከናውን መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አሰፋ÷ በኢትዮጵያ የሙስና ወንጀል የሀገር እድገት ፈተና በመሆኑ የመከላከል ስራው በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጸረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ባከናወናቸው ውጤታማ ተግባራትም 9 ቢሊየን ብር እና 4 ሚሊየን ካሬ ሜትር መሬትን ከሌብነት ማትረፍ ተችሏል ነው ያሉት።