ኢትዮጵያ አሁን ያላት አቅም የቫይረሱን ስርጭት መከላከልና መቆጣጠር ብቻ እንደሆነ ተገንዝቦ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ አሁን ያላት አቅም የቫይረሱን ስርጭት መከላከልና መቆጣጠር ብቻ እንደሆነ ተገንዝቦ መስራት እንደሚገባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መሪማሪ ቦርድ አሳሰበ።
መሪማሪ ቦርዱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር አስመልክቶ በሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የቫይረሱ ምላሽ አሰጣጥ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድጋፌ ጸጋዬ ለመርማሪ ቦርዱ ሪፖርት አቅርበዋል ፡፡
ባለሃብቶችንና ወጣቶችን በማስተባበር የአይነት እና የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ድጋፉ ለሚሹ የህብረተብ ክፍሎች መድረስ እንደቻለም ከንቲባው ጠቅሰዋል ፡፡
ቫይረሱን ከመከላከል ጎን ለጎን መደበኛ የልማት ስራዎች በተቀመጠላቸው እቅድ እየተከናወኑ መሆናቸውንም አቶ ድጋፌ ገልፀዋል።
በከተማዋ በቂ ለይቶ ማቆያዎችና ለጤና ባለሙያዎች አስፈላጊው ግብዓት እንደተሟላላቸውም ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጅ ለበርካታ ለከተማዋ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ቢሰጥም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አለመደረጉን ተናግረዋል ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢና የቡድኑ መሪ አቶ ተስፋዬ ዳባ በቀረበላቸው ሪፖርት ላይ ተመስርተው ግብረ ሃይሉ ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የቤት ለቤት ግንዛቤ የፈጠረ ቢሆንም የግንዛቤ መስጨበጫ ስራው ውጤት እንዳላመጣ ገልጸዋል ፡፡
የከተማዋ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዳላደረገ በምልከታቸው እንደታዘቡ አቶ ተስፋዬ ገልጸው ፣ ቫይረሱን ቀለል አድርጎ መገንዝብና መዘናጋቱ ሃያል ነን የሚሉ ሃገራትን በቀላሉ ማንበርከክ እንደቻለ ተናግረዋል ፡፡
ቫይረሱ ጠንካራ ኢኮኖሚና ዘመናዊ የጤና ተቋማት ያላቸውን ሃያል ነን የሚሉ ሃገራት ዜጎችን እንደቅጠል እያረገፈ ስለሚገኝና ሃያልነታቸው ህዝባቸውን ከሞት መታደግ እንዳላስቻላቸው ጠቅሰው ከእነሱ ድክመት በመማር ግብረ ሃይሉ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድርግ ህብረተሰቡ ከአስከፊው ቫይረስ ራሱን እንዲጠብቅ ማድረግ ይጠበቅበታል በማለት አሳስበዋል ፡፡
የተለያዩ ባለሃቶችንና ወጣቶችን በማስተበባር ድግፍ መሰብሰቡ፣ ቫይረሱን ከመከላከል ጎን ለጎን መደበኛ የልማት እንቅስቃሴዎች ሳይቋረጡ እየተከወኑ መሆናቸው ፣ በተሰበሰበው ድጋፍ አብዛኞቹ ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን የመርማሪ ቦርዱ አባላት በጥንካሬ አንስተዋል ፡፡
በሌላ በኩል ሰፊ የቤት ለቤት ግንዛቤ ማስጨበጫ ቢሰጥም ውጤት አለማምጣቱ ፣ ግብረ ሃይሉ እኩል ተራምዶ ቫይረሱን ለመከላከል አለማቻሉን መርማሪ ቦርዱ በድክመት ከጠቀሳቸው መካከል ይገኙበታል ፡፡
የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል በበኩሉ በመርማሪ ቦርዱ የተነሱ ትኩረት የሚሻቸውን ጉዳዮች መስዶ እንደሚሰራ ገልጾ፣ የውሃና መብራት፣ የታሪፍ መመሪያው ወጥ አለመሆን ፣ የትራንስፖርት እጥረት ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሆነ መግለፁን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዘናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።