ስፓርት

የብራዚሉ ክለብ ሳንቶስ ከ111 ዓመት በኋላ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን መውረዱ አነጋጋሪ ሆኗል

By Mikias Ayele

December 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በርካታ ከዋክብቶችን ያፈራው የብራዚሉ ክለብ ሳንቶስ ከ111 ዓመት በኋላ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን መውረዱ ደጋፊዎችን አስቆጥቷል፡፡

ሳንቶስ የክለቡ ወርቃማ ዘመን በተባለው  1950ዎቹ እና 60ዎቹ 12 የሀገራዊ ውድድር ክብሮችን፣6 የሊግ ውድድር ዋንጫዎችን እንዲሁም 2 የኮፓሊቨርታዶርስ ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደካማ አቋም እያሳየ የመጣው ሳንቶስ በብራዚል ሴሪ ኤ ማጠናቀቂያ ፎርታሌዛ በሜዳው 2 ለ 1 መሸነፉን ተከትሎ ከ111 አመታት በኋላ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ወርዷል፡፡

ክለቡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ያጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ ለክለቡ መውረድ ምክንያት ስለመሆኑም ነው የተገለፀው፡፡

በክለቡ መውረድ የተበሳጩት የሳንቶስ ደጋፊዎች የክለቡን አውቶብሶች ሲያቃጥሉ መስተዋላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሳንቶስ ፔሌ ፣ኔማር፣ሮዴርጎ ዳ ሲልቫ፣አሌክስ ሳንድሮ፣ዳኒሎ፣ፍሊፕ አንደርሰንን የመሰሉ የዓለማችን ከዋክብቶች ተጫውተው ማለፋቸው የሚታወስ ነው፡፡