አፍሪካ የኮቪድ 19 ስርጭት ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለፀች
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ የኮቪድ 19 ስርጭት ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የአፍሪካ ቻይና ትብብርን በተመለከተ የሰጡትን መግለጫ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ልኳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር ጠንከራ ግንኙነት እንዳላት በመጥቀስ ከነፃነት ትግል ጀምሮ ፤ በትብብርና በጋራ እስከመልማት የዘለቀ ግንኙነት እንደፈጠሩ ተናግረዋል።
ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት ያላቸው አፍሪካ እና ቻይና የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል በድጋሜ አብረው ቆመዋል ነው ያሉት።
ከ50 በላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ለቻይና መንግስት የአጋርነት መልዕክት በማስተላለፍ ከሀገሪቱ ጎን መቆማቸውን አስመስክረዋል ብለዋል።
ሀገራቸው ወደ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የህክምና ባለሙያዎችን በመላክ ለጤና ባለሙያዎች ስልጣና መሰጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንስተዋል ።
በዚህም ከ10 ሺህ በላይ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ልምድ እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል።
በቻይና ሁቤ እና ውሃን ከተማ የሚገኙ አፍሪካዊያን እንደዜጎቻችን እና እንደቤተሰቦቻችን ደህንነታቸውን የመጠበቅ ስራ ተከናውኗልም ብለዋል።
ወቅቱ የቻይና አፍሪካ ግንኙነት የሚፈተንበት ቢሆንም አሁንም እየተጠናከራ መሆኑን ያነሱት ዋንግ ዪ አፍሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በምታደርገው ጥረት የቻይና ድጋፍ እንሚቀጥል ጠቁመዋል።
የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል ዋና ፅህፈት ቤትን ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እንደሚሰራ የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ የህብረተሰብ ጤና አቅም ለማሻሻል ድጋፍ እንደሚደረግ አብራርተዋል ።
እንዲሁም የአፍሪካን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በድጋሜ ለመክፈት እና በሂደት ላይ የነበሩ የትብብር ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠልም ድጋፍ እንደሚደረግ ነው ቻይና ያስታወቀችው።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አፍሪካዊያንን ለመርዳት ሌሎች የሁለትዮሽ ድጋፎችን ለማድረግ ሀገራቸው በሂደት ላይ እንደምተገኝም ገልጸዋል።