ቢዝነስ

የጃፓን ቢዝነስ ልዑካን የአይሲቲ ፓርክን ጎበኙ

By Shambel Mihret

December 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓን ቢዝነስ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የአይሲቲና ዲጂታል ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችል ጉብኝት አደረገ፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሄኖክ አሕመድ÷ በአይሲቲ ፓርኩ የተፈጠረውን የኢንቨስትመንት መልካም ሁኔታና አማራጭ ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የጃፓን ቢዝነስ ልዑክ ቡድን አባላትም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ተዛማጅ ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ስለ ኢትዮጵያ እንዲሁም ስለ አይሲቲ ኢንቨስትመንት አማራጮችና የአይሲቲ ፓርክ የኢንቨስትመንት መዳረሻነት አስፈላጊ ያሏቸውን መረጃ ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ልዑኩ በፓርኩ ውስጥ በስራ ላይ ያሉትን ጨምሮ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉትን ድርጀቶችም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት እንደጎበኘ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡