የሀገር ውስጥ ዜና

አፍሪካውያን በዓለም መድረክ የጋራ ድምጻቸው እንዲሰማ በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ተባለ

By ዮሐንስ ደርበው

December 27, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካውያን በዓለም መድረክ የጋራ ድምጻቸው እንዲሰማ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ተባለ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴን ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ኢሲኤ ግንኙነታቸውን አጠናክረው በትብብር በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካውያን የጋራ ድምጽ በዓለም መድረክ እንዲሰማ በጋራ እንደሚሠሩም አቶ አሕመድ አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዕድገትና ልማቷን ለማፋጠን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳን ጨምሮ የተለያዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኗንም አብራርተዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካና በአፍሪካ አኅጉር ደረጃ የኢኮኖሚ ልማት ለማምጣትና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በቅርበትና በትብብር ትሠራለች ብለዋል፡፡

እንደ አፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ሊቀመንበርነታቸውም በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጎልበት ለሚደረገው ጥረት ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በጥምረት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው÷ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተቋቋመው ለአህጉሩ በመሆኑ አፍሪካውያን በዓለም መድረክ የጋራ ድምጻቸው እንዲሰማ ኢሲኤና የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የፕላንና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች 56ኛው ጉባዔ በኢሲኤ አዘጋጅነት መጋቢት 2016 ዓ.ም በዚምባብዌ እንደሚካሄድ ተጠቅሷል፡፡

ጉባዔውም ወደ አሳታፊና አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሚደረገውን ጥረት በገንዘብ የሚደገፍበት ሂደት ላይ ይመክራል መባሉን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!