ሃይማኖታዊ ክበረ በዓላት የመንፈሳዊ ልዕልና መገለጫ መድረኮች ናቸው – የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃይማኖታዊ ክበረ በዓላትና ስብስቦች የመንፈሳዊ ልዕልና መገለጫ መድረኮች እንጂ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ሊተላለፍባቸው አይገባም ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል ፡-
ሃይማኖታዊ ክበረ በዓላትና ስብስቦች የመንፈሳዊ ልዕልና መገለጫ መድረኮች እንጂ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ሊተላለፍባቸው አይገባም፡፡
ሃይማኖቶች የመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ዕሴት መሠረቶች በመሆን ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባርና የግብረ ገብነት ትምህርትና ግንባታ የሚከናወንባቸው ማዕከላት መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ሃይማኖታዊ ትዕዛዛትና አስተምህሮዎችም የሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነትና ቁርኝነትን በማጠናከር ሰላም፣ መከባበር፣ አብሮነት፣ ይቅርታ፣ እርቅ፣ ፍትህ እና የመሳሰሉ በጎ ዕሴቶችን በማስተማር ዘመናትን የዘላቀ አገልገሎት ሲሠጡ ኑረዋል፤ እየሠጡም ይገኛሉ፡፡ ይህም አገራዊ አንድነትን አስጠብቆ ለመዝለቅ አስችሏል፡፡
ከዚህም ባለፈ የሃይማኖት አባቶች ዋና ተልዕኳቸውና አገልግሎታቸው የሰው ሁለንተና ማገልገልና አማኞች ፈሪሀ ፈጣሪ አድሮባቸው የመንፈሳዊ ልዕልና እንዲጎናፀፉ ማድረግ ሲሆን ለዚህም ራሳቸውን ከዓለማዊ ጉዳዮችና ጣጣዎች በመራቅ እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት በምሳሌነት እየኖሩ አስተምህሮው የሚያዛቸውን በተግባር ገልጠዋል፡፡
የሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነትና መስተጋብርም የሰመረ እንዲሆን መንፈሳዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው በማስተማር፣ በመምከርና በመገሠፅ የአባትነት፣ የጠባቂነትና የመሪነት አደራቸውንና ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፤ እየተወጡም ይገኛሉ፡፡ በተለይም በመንግስታዊም ይሁን መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሚስተዋሉ በደሎችንና ኢፍትሐዊነቶች ሁሉ እንዲታረሙና እንዲስተካከሉ መጣር፣ አጥፊዎችም ከስህተታቸው እንዲታረሙ በፍቅር መገሰፅ ሃይማኖታዊና የተለመደ አሠራር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገብል እንላለን፡፡
ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ከዚህ መሠረታዊ ተልዕኮና ዓላማ በማይስማማ አኳኋን ለሃይማኖታዊ ተግባርና ዓላማ በሚደረጉ ስብስቦች እና በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ተገቢ ያልሆኑና በአብዛኛው ፖለቲካዊ ይዘት የጎላባቸው፣ አገር አፍራሽና ደም አፋሳሽ ስብከቶችና ትንታኔዎች ሲነገሩ እንመለከታለን፡፡
ስብከቶቹና ንግግሮቹ ፖለቲካውና ፖለቲከኞችን የሚተቹ ወይም የሚደግፉ ከመሆናቸው በላይ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ የመቀስቀስና የማነሳሳት አዝማሚያ የሚታይባቸው መሆኑ ጉዳዩ ከየትኛው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጋር የማይስማማና ድጋፍም የሌለው መሆኑ ደግሞ የስብከት ልምምዱ አደገኛና በእጅጉ የሚወገዝ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ስብከትና አካሄድም የሰላም፣ የመከባበርና የአብሮነት ዕሴቱን የሚጎዳ በመሆኑ በአፋጣኝ ሊታረም ይገባል፤ የሃይማኖት ተቋማትም እንዲህ ዓይነት ስብከት የሚሠብኩና የሚናገሩ አባቶችን፣ አስተማሪዎችን ወይም ሰባኪ አገልገዮችን እንዲታረሙ የማድረግ ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መንፈሳዊ ልዕልናን እንዲያሰፍኑ ጭምር ጉባኤያችን በአጽንኦት ያሳስባል፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!