Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ አፍሪካ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ጥሪ ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲው በደቡብ አፍሪካ እና በደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ለሚገኙ የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ይፋ ማድረጊያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር)፣ ዳያስፖራዎች፣ በደቡብ አፍሪካ የተባበሩት የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ማህበር፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሚዲያ አካላት፣ የከፍተኛ ምሁራን እና የሴቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር፥ መላው 2ኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በመጓዝ ስለሀገራቸው ባህልና ታሪክ እንዲያውቁና እንዲተሳሰሩ፣ የሀገር ፍቅር ስሜታቸውን እንዲያጎለብቱና በሀገረመንግስት ግንባታና የልማት እንቅስቃሴዎች አሻራቸውን እንዲያሳርፉ በጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አሕመድ የቀረበው ጥሪ ታሪካዊ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡

በደቡባዊ አፍሪካ ለሚገኙ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አባላትም ጥሪውን በመቀበልና ወደ ሀገር ቤት በመጓዝ ተጨባጭ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪውን በይፋ አቅርበዋል፡፡

ጥሪውን በመቀበል ወደ ሀገር ቤት ለሚጓዙ የዳያስፖራ አባላት ስኬታማ ቆይታ እንዲኖራቸው አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁንም ነው የተናገሩት፡፡

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የዳያስፖራ የአደረጃጃት ተወካዮች እና የሁለተኛ ትውልድ ወጣት የዳያስፖራ አባላት በበኩላቸው፥ ጥሪው የሀገር ፍቅርን የሚቀሰቅስና የባለቤትነት ስሜትን የሚያጎለብት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመጀመሪያ ዙር የሀገር ቤት ግቡ ጥሪ ወቅት የሰጡትን ተጨባጭ ምላሽ ለመድገምና ወደ ሀገር ቤት በመጓዝ በተዘጋጁት ሁነቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁነታቸውንም ነው ያረጋገጡት፡፡

በሌላ በኩል ከሀገራዊ ጥሪው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በደቡብ አፍሪካ በፈረንጆቹ 2023 የትምህርት ዘመን በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችና ወላጆች የእውቅና የማበረታቻ መስጠት መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በወቅቱም የላቀው ውጤት ያስመዘገቡ 50 ወጣት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የእውቅናና የምስክር ወረቀትና የስጦታ ሽልማት በአምባሳደር ሙክታር(ዶ/ር) ተበርክቶላቸዋል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.