አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የኮሙኒኬሽን ስልጠና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የኮሙኒኬሽን ስልጠና መሰጠቱን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ነው ለኮሙኒኬሽን ባለሞያዎቹ በዲጂታል ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን የሥራ ሒደት ላይ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሥልጠና የሰጠው፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ክልሉ ከነበረበት ቀውስ በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ለክልሉ መረጋጋት የኮሙኒኬሽን ባለሞያዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ መስራት ውጤታማ እደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው÷ስልጠናው ሰላምን፣ ልማትና ሀገራዊ ብልፅግናን ጊዜውን በሚመጥን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እየታገዙ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲያደርጉ አቅም እንደሚፈጥር አመላክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ሥልጠናው የክልሉን የኮሙኒኬሽን አቅም ለማዳበር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው መግለጻቸውን የኢንስቲትቱ መረጃ ያመላክታል፡፡