በሐረሪና ሶማሌ ክልሎች የትምህርት ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ተከናውነዋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ እና ሶማሌ ክልሎች የትምህርት ተደራሽነትን እና ጥራትን የሚያረጋግጡ ተግባራት መከናወናቸው ተገለጸ፡፡
የሶማሌና ሐረሪ ክልሎች ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷ የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት ደረጃቸውን የጠበቁ የትምህርት ቤቶች ግንባታ ማከናወንና የመምህራን አቅምን የማሳደግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በክልሎቹ ህብረተሰቡንና አጋር አካላትን በማሳተፍ በተሰሩ ስራዎች የትምህርት ተደራሽነትን የሚያሰፉ በጎ ተግባራት ተከናውነዋልም ተብሏል።
የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙባረክ ሀሰን ÷ በክልሉ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በዓይነት፣ በገንዘብ፣ በጉልበት እና በእውቀት ጭምር ወደ 48 ሚሊየን ብር ማሰባሰብ ተችሏል ነው ያሉት።
በክልሉ በተለያዩ 6 ወረዳዎች 6 ሞዴል የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸው በመግለጽ በቀጣይ በሌሎች ወረዳዎችም ተጨማሪ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ ጠቁመዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ትመህርት ቢሮ ኃላፊ አብዲላሂ አብዲ በበኩላቸው ÷ በክልሉ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር 190 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል ነው ያሉት።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት ከ100 በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደተገነቡ ጠቅሰው ÷ 12 አዳሪ ትምህርት ቤቶች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
ከ500 በላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጥገና፣ ማስፋፋት እና እንደአዲስ ተገንብተዋልም ተብሏል፡፡
ከአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ መደረግ ጋር ተያይዞ በሶማሌ ክልል ለትምህርት ዘመኑ የሚያስፈልጉ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ መጽሓፍት ታትመው የማሰራጨት ስራ መሰራቱም ነው የተገለጸው፡፡
በመራኦል ከድር