Fana: At a Speed of Life!

በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መረጃዎች እንዲደርሷቸው ከኤምባሲዎች ጋር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አባላት መረጃዎች እንዲደርሷቸው ከኤምባሲዎች እና ቆንፅላዎች ጋር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
 
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁለተኛው ምዕራፍ ሀገራዊ ጥሪ በውጭ ሀገራት የሚገኙ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው ተፈጥሮ፣ ባህል እና ታሪክ እንዲያውቁ ዓላማ ያደረገ ነው፡፡
 
የሀገር ፍቅር ስሜታቸው እንዲዳብር እና ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ትስስር እንዲጠናከር በማድረግ ለሀገራቸው እድገት አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱም የሚያስችል እንደሆነ ተመላክቷል።
 
ይህ ታላቅ ሀገራዊ ጥሪ የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከኤምባሲዎች እና ቆንፅላዎች ጋር ውይይት በማድረግ ውጤታማ እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ነብዩ ሰለሞን ተናግረዋል።
 
ጥሪው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በወጣው መርሃግብር መሰረት የሚተገበር መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጠቁመዋል።
 
በትውልዶች መካከል ድልድይ በመገንባት ወላጆቻቸው የገነቧትን ሀገር እንዲያውቁና ሀገር ቤት ከሚኖረው ማህበረሰብ ጋር በመገናኘት ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ማጠናከሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
 
ከዚህ ባሻገር በሀገር ቤት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ባህላዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ቁርኝት እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል ነው ያሉት ተጠባባቂው ዳይሬክተሩ።
 
ጥሪ የቀረበላቸው በውጭ የሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መጥተው ሀገራቸውን እንዲያውቁና እንዲያለሙ ጠይቀዋል።
 
በሀገር ቤት ያለው ህዝብም፥ የእህት ወንድሞቹ ቆይታ ያማረና ሰላማዊ እንዲሁም ተመልሰው በትዝታ የሚያወሩት እንዲሆን የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
 
በመራኦል ከድር
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.