ሕብረተሰቡ በገና በዓል እሳትና ኤሌክትሪክ ኃይል ሲጠቀም ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕብረተሰቡ የፊታችን እሁድ ከሚከበረው የገና (ልደት) በዓል ጋር በተያያዘ እሳትና የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮችን ሲጠቀም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
ሁሉንም ሥራዎች በተመሳሳይ ጊዜ ጎን ለጎን ለመሥራት መሞከር ድካም የሚያስከትልና ትኩረትን የሚያሳጣ በመሆኑ ለአደጋ እንደሚያጋልጥ በመረዳት ከዚህ ድርጊት መቆጠብ እንደሚገባ ኮሚሽኑ መክሯል፡፡
በአንጻሩ እንደቤተሰብ አባል ብዛትና ችሎታ ሥራን በመከፋፈል በቅደም ተከተል ማከናወን እንደሚገባም ነው የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡
በሌላ በኩል ከበዓል ጋር ተያይዞ ሻማ በሚለኮስበት ጊዜ ሻማው ከተቀጣጣይ ቁሶች መራቁን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው÷ ከቤት ሲወጡም ሻማውን መጥፋቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ለበዓሉ ድምቀት ታስበው የሚዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮች ካሉም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲያልፍ ሕብረተሰቡ ከኮሚሽኑ የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እንዲተገብርም ጠይቀዋል፡፡
ጥንቃቄዎችን አልፎ ለሚያጋጥም አደጋ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ስላደረገ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል አደጋዎች ሲያጋጥሙ ሕብረተሰቡ በነፃ የስልክ መስመር 939፣ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 0111555300 ወይም በ 0111568601 በመደወል ለኮሚሽኑ እንዲያሳውቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!