Fana: At a Speed of Life!

ሕብረተሰቡ በበዓል ሰሞን ሊፈጸሙ ከሚችሉ ወንጀሎች ራሱን እንዲጠብቅ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕብረተሰቡ በመጪዎቹ በዓላት ሊፈጸሙ ከሚችሉ የማታለል እና የማጭበርበር ወንጀሎች ራሱን እንዲጠብቅ ፖሊስ አሳሰበ፡፡

በኢትዮጵያ በበዓላት ሰሞን ሁሉም የቤቱን አቅም ግምት ውስጥ ያስገባ ግብይት መፈጸሙ የተለመደ ተግባር ነው፡፡

በበዓላት የግብይት ወቅትም በርካቶች በተለያየ መንገድ ለዝርፊያ እንደሚጋለጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ም/ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

ይህን ታሳቢ በማድረግም በመዲናዋ በመገበያያ፣ ትራንስፖርት መጠበቂያ እና በዋና ዋና አደባባዮች ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመከላከል ፖሊስ አስተማማኝ ዝግጅት ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡

ለዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው የፖሊስ አባላት በክፍለ ከተማ፣ ወረዳ እና ቀጠና ድረስ ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ስምሪት መሰጠቱን አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ቴክኖሎጂው ከመዘመኑ ጋር ተያይዞ የማታለያ መንገዶች ውስብስብ እየሆኑ በመምጣታቸው ወንጀሎችን ፖሊስ ብቻውን ሊከላከላቸው እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በዲጂታል ባንኪንግ በሚፈጸም ግብይት ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ነው ያሳሰቡት፡፡

ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የሀሰተኛ ገንዘብ ሥርጭት በተለይም በእርድ እንስሳት ገበያዎች አካባቢ ሊኖር እንደሚችል አስገንዝበዋል።

በሚበሉና በሚጠጡ ግብዓቶች ላይ ባዕድ ነገር ቀላቅለው በርካሽ ዋጋ የመሸጥ ሁኔታ በበዓል ገበያ ወቅት እንደሚስተዋልም ጠቁመዋል።

በመዝናኛ ስፍራዎች ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት እንደሚገባም ም/ኮማንደሩ አስገንዝበዋል።

በበዓል ወቅት ጠጥቶ ማሽከርከር የሚያስከትለው ቀውስ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፥ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በበዓል ሰሞን የሚከሰቱ የማታል፣ የንጥቂያ፣ ማጭበርበር እና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በቅንጅት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

ነዋሪዎች በየትኛውም ሁኔታ መሰል ወንጀሎችና አጠራጣሪ ነገር ሲመለከቱም በስልክ ቁጥር 011 111 0111 ወይም በ991 በመደወል ጥቆማ መስጠት ይችላሉም ነው ያሉት።

በመላኩ ገድፍ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.