ገና በሚከበርባት የላሊበላ ከተማ በ23 ዓመታት የታነጹት ቤተ-መቅደሶች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት (ገና) በዓል በልዩ ሁኔታ በሚከበርባት ላሊበላ ከተማ በሦስት ምድብ የታነጹ የተለያዩ ቤተ-መቅደሶች ይገኛሉ፡፡
በየዓመቱ ታኅሣስ 29 የገና በዓል በላሊበላ ከተማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ-ክርስቲያን ተከታዮች እንዲሁም ጎብኚዎች በተገኙበት ይከበራል፡፡ (ታኅሣስ 29 የሚውለው ልደት በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ በታኅሣስ 28 ይውላል)
ከዚህ ቀን ቀደም ብሎ በተለያዩ ቤተ-ክርስቲያኖች ሐይማኖታዊ ሥርዓቶች ይቀርባሉ፡፡
የገና በዓል በላሊበላ በልዩ ሁኔታ የሚከበረው አንድም፥ ከአንድ አለት የተፈለፈሉት ቤተ-መቅደሶች የኢየሩሳሌም ምሳሌ (ዳግማዊት ኢየሩሳሌም) ተብለው በሐይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ስለሚታመን ነው፡፡
በዚህም ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ ሁኔታዎች ያልፈቀዱላቸው አማኞች እንዲሁም ጎብኚዎች ወደ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም (ላሊበላ) በማቅናት መንፈሣዊ ሥርዓታቸውን ይፈፅማሉ፤ በረከትም ያገኛሉ፡፡
ሌላው ደግሞ ቤተ-መቅደሶቹን ያነጸው ቅዱስ ላሊበላ እና ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለዱበት ዕለት ተመሳሳይ (ታኅሣስ 29) መሆኑ ነው፡፡
ቅዱስ ላሊበላ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን ቤተ-መቅደሶች ለማነጽ 23 ዓመታት እንደፈጀበትም ይነገራል፡፡
ኪነ-ሕንጻውም በምድራዊት ኢየሩሳሌም፣ በሰማያዊት ኢየሩሳሌም እና በኖኅ መርከብ ምሳሌ ተደርጎ መታነጹም ይታመናል፡፡
በሕንጻ ግንባታ ቅደም ተከተላቸው መሠረትም በምድብ አንድ በምድራዊት ኢየሩሳሌም የሚመሰሉት፥ ቤተ- ማርያም፣ ቤተ-መድኃኒዓለም፣ ቤተ-ጎልጎታ (ቤተ-ሚካኤል)፣ ቤተ-መስቀል እና ቤተ-ደናግል ናቸው፡፡
አቀማመጣቸው መስቀለኛ መሆኑን እና ልክ ክርስቶስ ሲሰቀል የተቸነከሩት ችንካር (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናስ፣ አዴራ ሮዳስ) እንደሚባሉ በእነዚህ አቀማመጥ ልክ ይገኛሉ፡፡
በምድብ ሁለት የሚገኙት እና በሰማያዊት እየሩሳሌም የሚመሰሉት ደግሞ፥ ቤተ-ገብርዔል፣ ቤተ-አማኑኤል፣ ቤተ- መርቆርዮስ፣ ቤተ-አባ ሊባኖስ መሆናቸውን እና አራቱም በአንድ አቅጣጫ እንደሚገኙም ይታወቃል፡፡
እንዲሁም በምድብ ሦስት ለብቻው የሚገኘው እና በኖኅ መርከብ ምሳሌ ተደርጎ የታነጸው የቅዱስ ላሊበላ የመጨረሻ ሥራ የሆነው ቤተ-ጊዮርጊስ ነው፡፡
ቤተ-ጊዮርጊስ የአራቱ አቅጣጫዎች አመላካች ኖሮት በመስቀለኛ ቅርጽ የታነጸ ቤተ-መቅደስ ነው፡፡
ቅዱስ ላሊበላ ታኅሣስ 29 ቀን 1101ዓ.ም ተወልዶ፥ ከ1157 እስከ 1197 ለ40 ዓመታት በንግሥና ቆይቷል፡፡
በ1157 ዓ.ም ከቅዱስ ገብረ ማርያም ንግሥናውን ከተቀበለ በኋላ፥ ከ1166 እስከ 1189 ለ23 ዓመታት 10 ቤተ- መቅደሶች አንጿል፡፡
ኢትዮጵያውያን ቅዱስ ላሊበላ ያነጻቸውን ድንቅ ቤተ-መቅደሶች ጨምሮ ከላሊበላ ከተማና ላስታ ወረዳ የሚገኙትን ይምርሐነ-ክርስቶስ፣ ነአኩቶለአብ እንዲሁም አሸተን (አሽተን) ማርያምን በመጎብኘት የኢትዮጵያን ታሪክና ጥበብ ተረድተው ለሌሎች የማሳወቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎችም ከበዓሉ መከበር ቀደም ብለው የሚመጡ እንግዶቻቸውን በአካባቢው የእንግዳ አቀባበል ወግ መሰረት እግር አጥበው ይቀበላሉ፤ ማረፊያ ይሰጣሉ፤ ቤት ያፈራውን እህል ውሃ ያቋድሳሉ።
ነገ የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ የልደት በዓል በላሊበላ ከተማ በድምቀት ይከበራል፡፡
መልካም በዓል!!
በዮሐንስ ደርበው