የሰላም ጥሪው ሕዝብና መንግሥትን ያግባባ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት በአማራ ክልል ያቀረበው የሰላም ጥሪ ሕዝብ እና መንግሥትን ያግባባ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡
በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪና የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው በወቅታዊ የክልሉ ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም÷ የክልሉ ሰላም በየጊዜው ለውጥ እያመጣ በእጅጉ እየተሻሻለ ነው ብለዋል።
የመልካም አሥተዳደር፣ የትራንስፖርት፣ የንግድ ሥራዎች እና አገልግሎቶች ተስተጓጉለው እንደነበርም አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ከነበረው መስተጓጎል በመውጣት ወደ መደበኛ ሥራዎች መገባቱንም ነው ያስታወቁት፡፡
የክልሉ ሰላም እንዲመለስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያበረከተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ ባልተገባ ፕሮፖጋንዳ የተናጋው ሰላም እና የተሳሳተው አካሄድ ሁሉ እየተሻሻለ መጥቷል፤ የክልሉ የፀጥታ መዋቅርም ተጠናክሯል ብለዋል፡፡
የክልሉ ሰላም በእጅጉ መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ሙሉ ለሙሉ የሕዝብን ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል ማለት እንደማይቻል ጠቅሰው÷ በአንዳንድ አካባቢዎች ማኀበረሰቡ አሁንም እየተጎሳቆለ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በቀጣይም የተጀመረውን ሰላም ማፅናት እና ዘላቂ ማድረግ ይጠበቃል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
በጋራ አንድነት የተመሠረተች ኢትዮጵያን የመገንባት ሂደቱ እንዲጠናከር ከሕዝቡ ጋር እየሠራን ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሥራ አጥነት ችግሮች እንዲፈቱ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ አሁንም ሕዝቡ እየሠራ ነው፤ በቀረበው የሰላም ጥሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላም በመምጣት ስልጠና እየተሰጣቸው ነው ብለዋል፡፡
የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ሰላም የገቡት የጦር መሳሪያቸውን በመደበኛነት አስመዝግበው እንዲይዙ እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ጠንካራ የፀጥታ ተቋም የመገንባት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲከውኑ እየተሠራ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
አሁንም ጥቂት አካላት የሕዝብ ሰላም እንዲናጋ እየሠሩ እንደሆነ ጠቅሰው÷ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
በዓላትን ለማጠልሸት የሚሠሩ ሥራዎች ተገቢ አይደሉም፤ በዓሉን ለማወክ የሚሠራ ካለም አይሳካለትም ብለዋል።
በኃይል የሚሳካ ነገር የለም፤ ይህን አውቆ ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC(Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!