Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የገናና ጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት በሰላምና በድምቀት እንዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ የሚዲያ ዋና ክፍል ሃላፊ ም/ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ÷ በክልሉ ገናና ጥምቀትን ጨምሮ ሌሎች በዓላት በሰላም እንዲከበሩ እስከ ታችኛው መዋቅር ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በዓላቱን ያለ ምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር በክልሉ ከሚገኘው ኮማንድ ፖስት ጋር በልዩ ሁኔታ በትኩረት እና በትብብር መስራቱን ነው የገለጹት፡፡

ገናና ጥምቀትን ለማክበር የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ወደ ክልሉ እንደሚመጡ ጠቁመው÷ እንግዶቹ በዓላቱን በሰላም እንዲያከብሩና የቆይታ ጊዜያቸው እንዲሰምር በቅንጅት ተሰርቷል ብለዋል።

በላሊበላ የሚከበረው የገና በዓል ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ የክልሉ ጸጥታ አካላት ከወጣቶች፣ ከመከላከያ ሠራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ አባላት ጋር ልዩ ሥምሪት እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

በጎንደር የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር የከተማዋ ወጣቶች እና የእምነት አባቶች ከፍተኛ ድርሻ ወስደው ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የክልሉ እና የፌዴራል ጸጥታ አካላት ያለውን ነባራዊ የጸጥታ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ዝግጅት እንዳደረጉ ም/ኮማንደሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ከበዓላት አከባበር ጋር በተያያዘ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችን ቀድሞ በመለየት በብቃት ማክሸፍ የሚያስችል ስምሪት መሰጠቱን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሕብረተሰቡም ማንኛውንም አጠራጣሪ ጉዳይ ሲመለከት በአቅራቢያ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት እንዲሳውቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.