4ኛው ፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በታሪኩ በከፍተኛ የሽልማት መጠን ዛሬ ይጀምራል
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው 4ኛው ፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በታሪኩ በከፍተኛ የሽልማት መጠን ዛሬ በገና በዓል ዋዜማ በቀጥታ ሥርጭት እንደሚጀመር ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቋል፡፡
ውድድሩ÷ የፋና ላምሮት ምዕራፍ 13፣ ምዕራፍ 14 እና ምዕራፍ 15 አሸናፊዎችን ያገናኛል።
በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6:00 ሰዓት ጀምሮ የምድብ አንድ 8 ተወዳዳሪዎች ከዛየን ባንድ ጋር በሁለት ዙሮች ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ።
የዚህኛውን የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በአንደኛነት ለሚያጠናቅቅ ተወዳዳሪ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሽልማት አዘጋጅቷል።
በአጠቃላይ ለሽልማት የሚውል 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ማዘጋጀቱንም ነው ተቋሙ ያስታወቀው፡፡
ዛሬ የሚጀመረውን የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ተመልካቾች ከ6:00 ሰዓት ጀምሮ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች፣ በፋና ቴሌቪዥን እና በኤፍም ኤም 98 ነጥብ 1 በቀጥታ ሥርጭት እንዲከታተሉ ተጋብዘዋል፡፡
ተመልካቾችም በ8222 የስልክ መስመር አጭር የጽሑፍ መልዕክት በመላክ በንቃት ይሳተፋሉ፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተሰጥኦ ኖሯቸው ዕድሉን ያላገኙ ድምፃውያንን ወደመድረክ በማምጣት እንዲሁም ለሙዚቃው ዘርፍ ዕድገት የራሱን ዐሻራ ለማሳረፍ የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በለምለም ዮሐንስ