በሐረሪ ክልል ለበዓል መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች እጥረት እንዳይከሰት ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገና በዓል ላይ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችና የምርት እጥረት እንዳይከሰት ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ መሆኑን የሐረሪ ክልል ንግድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በዓሉን በተመለከተ በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰትም የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ሸሪፍ ሙሜ እንደገለጹት÷ ህብረተሰቡ በዓልን ሲያከብር መቸገር የለበትም።
በከተማው ምርቶች በነጋዴው እና በሸማቾች ማህበራት በኩል ቀርበው በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሸጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
እየቀረቡ ከሚገኙ ምርቶች መካከል የምግብ ዘይት፣ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች እንደሚገኙባቸው አመላክተዋል።
በክልሉ በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ለመከላከል የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ ቀጥሏል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በሽንኩርት ዋጋ ላይ ያልተገባ ጭማሪ ባከናወኑ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱም ተገልጿል፡፡