Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአቅመ ደካሞችን ቤት አድሶ ለባለቤቶቹ አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአራዳ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 4 ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ባለሰባት ክፍል የመኖሪያ ቤት አጠናቆ ከሙሉ የቤት እቃ ጋር አስረከበ፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ቤቶቹን ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ባስረከቡበት ወቅት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚከናወኑ በርካታ የልማት ስራዎች መካከል መካከል የሰው ተኮር የልማት እንቅስቃሴ አንዱ ነው ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ካለው ውስን ሀብት አብቃቅቶ አራት ቤቶችን አድሶ ለባለቤቶቹ ማስረከቡን ገልጸዋል።

ይህ የሰው ተኮር ማህበራዊ አገልግሎት በዚህ የሚቆም እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ ወደፊትም እጅ ለእጅ ተያይዘን ቀጣይ የልማት ስራዎችን እንሰራለን ሲሉ መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመልክቷል።

እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በደምና በታሪክ የተሳሰርን፣ የምንጋራቸው የጋራ እሴቶች ያሉን በመሆናችን ይህን የመሰለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱ በሕዝቦች መካከል ወገን፣ አለኝታና ደጋፊ አለኝ የሚለውን ስሜት ያጠናክራል ብለዋል።

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእርስ በርስ ትስስር በማጎልበት አንዱ ለሌላው አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን በግልጽ ማሳየት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

እድሳት የተደርገላቸውን ቤቶች የተረከቡት አቅመ ደካሞች ለተደረገላቸው የቤት እድሳትና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የቤት እድሳት የተደረገላቸው ሦስት እናቶችና አንድ አባት አቅመ ደካማዎች ሲሆኑ በአጠቃላይ 25 ቤተሰቦች ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.