Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን የመስህብ ስፍራዎች በመጎብኘት ለዓለም ለማስተዋወቅ ዝግጁ ነን – 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የመስህብ ስፍራዎች በመጎብኘት ለዓለም ለማስተዋወቅ ዝግጁ ነን ሲሉ በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ተናገሩ፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እና የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከትላንት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ሲሆን ፥ በዛሬው ዕለትም ከተለያዩ ሀገራት ገብተዋል።

ዛሬ ከመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን መካከል ከካናዳ ቶሮንቶ የመጣው ወጣት ምንተስኖት ጌታቸው ፥ ከረጅም ጊዜ በኋላ ኢትዮጵያን ለማየት በመቻሌ ትልቅ ደስታ ተስምቶኛል ፤ ጉጉቴም እውን ሆኗል ብሏል፡፡

ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያን በምችለው ሁሉ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ሲልም ወጣት ምንተስኖት ተናግሯል፡፡

ሌላው ከካናዳ ቶሮንቶ የመጣው ሚላንድ ሬድዋን በበኩሉ ፥ በኢትዮጵያ አዲስ የተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጨምሮ በርካታ ቦታዎች መኖራቸውን ሰምቻለው ፤ ይሄንን ለማየት ዕድል በማግኘቴም ደስ ብሎኛል ነው ያለው።

በቀጣይም የቱሪስት ቦታዎችን በመሄድ ለመጎብኘት ተዘጋጅቻለሁ ማለቱን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

በውጭ የሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ አባልና የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ፥ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር በሚደረገው ጥረት በውጭ ያሉ ዳያስፖራ አባላት እውቀት፣ ሀብት ወሳኝ ሚና አለው።

በመሆኑም በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ያላቸውን እውቀትና ኃብት ተጠቅው ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

እንደጉምሩክ ኮሚሽንም ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው የሚመጡ ሁለተኛ ትወልድ ኢትዮጵያውያን ሲገቡ ችግር እንዳይገጥማቸው ቀልጣፋ አሰራሮች ተዘርግተዋል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.