Fana: At a Speed of Life!

ርዕሳነ መስተዳድሮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሳነ መስተዳድሮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የይቅርታ፣ የእርቅ እና ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሸጋገር ምልክት ነው ብለዋል፡፡

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያንም በዓሉ የፍቅር፣ የሰላምና የደስታ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ÷ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ “እንኳን ለ2016 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ፤በዓሉ የሠላም፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ እንዲሆንልን እመኛለሁም” ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ÷ ”የኢየሱስ ክርስቶስ የመወለዱ ሚስጥር የሰው ልጆችን ከጨለማው ዓለም የባርነት ሕይወት ነጻ ለማውጣትና የዘለዓለምን ሕይወት ለመስጠት የታለመ ነው” ብለዋል፡፡

“ኢየሱስ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ምሳሌያችን እንደሆነ ሁሉ እኛም ከጥላቻ ይልቅ ሰላምንና አንድነትን ብንናፍቅ ለሀገራችን ይበጃል” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷ በዓሉ በተለይም ዘንድሮ ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር በብዙ ድሎቻችን ታጅቦ፣ በኢትዮጵያዊነትና ህብረብሔራዊ አንድነት ደምቆ እንደሚከበር አንስተዋል፡፡

የገና በዓል የእምነቱ ተከታዮች የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን የበለጠ የሚያጠናክሩበት ሊሆን እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር (ኢ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፥የእምነቱ ተከታዮች የክርስቶስን ልደት ሲያከብሩ በኃይማኖታዊ አስተምህሮ መሠረት በልደቱ ያገኙትን በረከትና መዳን በተግባር በማሳዬት ሊሆን ይገባል።

ሠላምና ፍቅርን በመስበክ ብቻ ሳይሆን፣ በተግባርም የሠላም ባለቤት በመሆን ለሀገር ዕድገትና ሠላም በአንድነት መትጋት ይጠበቃል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው÷”የገና በዓልን ስናከብር በፈርሃ ፈጣሪ የታነፀ የመንፈስና የሞራል ስብዕናን በመጎናፀፍ ሠላምን፣ አብሮነትንና ወንድማማችነትን በማጠናከር መሆን ይገባዋል” ብለዋል።

ክልሉ በይፋ ተመስርቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት ላይ መሆኑ የዘንድሮውን የገና በዓል የተለየ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፥ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈው ÷ በዓሉ የፍቅር፣ የሰላምና የደስታ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

በዓሉ ሲከበርም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እና ወንድማማችነትን፣ አብሮነትንና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ መሆን እንዳለበት ተመላክቷል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-(Fana Broadcasting Corporate S.C.) t
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.