ሕብረተሰቡ ከእርድ የሚገኘውን ቆዳና ሌጦ በጥንቃቄ አዘጋጅቶ ለገበያ እንዲያቀርብ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለገና እና ጥምቀት በዓላት ከሚፈጸም እርድ የሚገኘውን ቆዳና ሌጦ በጥንቃቄ በማዘጋጀት በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ እንደሚገባ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አሳሰበ፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ በዓላት ወቅት ከሚፈጽም እርድ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊኖረው የሚችል የቆዳና ሌጦ ምርት እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ በበዓላት ወቅት ከእርድ የሚገኝን ቆዳ በጥንቃቄ አዘጋጅቶ በወቅቱ ለገበያ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንደሚስተዋል ማዕከሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡
ህብረተሰቡ በበዓላት ጊዜ በሚፈጽመው እርድ ወቅትና ከእርድ በኋላ ለቆዳና ሌጦ የሚያደርገው ጥንቃቄ እና ትኩረት እየቀነሰ መምጣቱም ተጠቁሟል፡፡
ይህን ችግር በመቅረፍ ለሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች የቆዳና ሌጦ ፍላጎትን ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እና የሥራ ዕድል ለማሳደግም ከሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ስለሆነም ማሕበረሰቡ ለገና እና ጥምቀት በዓላት በሚከናወን እርድ ወቅት ለቆዳ ጥራት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግም ነው ማዕከሉ ያሳሰበው፡፡
በዚህ መሰረትም ቆዳው ሲገፈፍ በቢላዋ እንዳይበሳ ፣ እንዳይቆሽሽና እንዳይበሰብስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡
የእርድ እንስሳትን በዱላ አለመምታት፣ የእርድ ቦታን ንፁህ ማድረግ እና ቆዳ ሲገፈፍ የተፈጥሮ መስመርን ተከትሎ መሰንዘር አስፈላላጊ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡
ህብረተሰቡ ቆዳውን በጥንቃቄ ካዘጋጀ በኋላም በወቅቱ ወደ ገበያ በማውጣት በየአካባቢው ቆዳና ሌጦ ለሚሰበስቡ አካላት እንዲያስረክብም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በመላኩ ገድፍ