አቶ አደም ፋራህ ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍስሃ፣ የቸርነትና የልግስና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል ፡-
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለገና በአል በሰላም አደረሳችሁ።
በአሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍስሃ፣ የቸርነትና የልግስና እንዲሆንላችሁ ምኞቴ ነው።
ይህ በአል የሚከበርበት ወቅት ሀገራችን የባህር በር ጥያቄዎቿ በተሳካ የዲፕሎማሲ ጥረት ምላሽ እያገኙ፣ከእዳ ወደ ምንዳ ለመስፈንጠርና ከምርጫ ማግስት ለህዝባችን ቃል የገባናቸውን ኪዳኖች ለመፈፀም እየተጋን፣ እንደ ሀገር የገጠሙንን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እየፈታን ባለንበት ሁኔታ ላይ ሆነን የሚከበር በአል በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
በአሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችን በመርዳት፣አቅመ ደካሞችን በመንከባከብ፣የታረዙትን በማልበስ፣ቤታቸው የጎደለ ድሆችን አይዟችሁ በማለት፣ካለን እና ቤታችን ካፈራው ላይ በማቋደስ፣ ፍፁም በሆነ መተሳሰብ በሞላው ኢትዮጵያዊ የጨዋነት መንፈስ ሊሆን ይገባል።
ይህን ማድረጋችን አንድም በፈጣሪ ዘንድ ቸሮታን የሚያስገኝልን ሲሆን አንድም ሰብአዊነትን በህብረተሰባችን ዘንድ በማሳደግ የሞራል ልእልናችንን ከፍ የማድረግ አቅም ስላለው ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በአሉን በመተሳሰብ እንድታከብሩት አደራ ማለት እፈልጋለው።
በተለይም ከ12 ሚሊየን በላይ የሚሆን አባል ያለው ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነው የብልፅግና ፓርቲ አባል የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን እናንተን በልዩ ሁኔታ አደራ ማለት የምፈልገው ይህንኑ ነው።
በበአላት ወቅት መረዳዳት መተሳሰብ እና መደጋገፍ ሰው ተኮር የሆነው የፓርቲያችንን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ያስችለዋልና በዚህ በአል ላይ በስፋት በበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ላይ እንድትሳተፉ አደራ ማለት እፈልጋለው።
የአንዳችን ቁስል በአንዳችን ካልተደፈነ፣የአንዳችን ቀዳዳ በአንዳችን ካልተሰፋ፣የአንዳችን ስብራት በአንዳችን ካልተጠገን ብቻችን ብንደምቅ ዋጋ የለውምና በአሉ በሀምራዊነት ተሸምነን የምንንፀባረቅበት፣በቸርነትን እና በልግስና የሚገኘውን በረከት በጋራ የምንቋደስበት ሊሆን ይገባል።
በድጋሚ እንኳን ለገና በአል በሰላም አደረሳችሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያ እና ውብ እሴቶቿን አብዝቶ ይባርክ ።
መልካም በዓል!!
አቶ አደም ፋራህ
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ፅ/ቤት ኃላፊ