የመዲናዋ ሆቴሎች ለ2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው እንግዶችን እየተቀበሉ ነው
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሆቴሎች በውጭ የሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንን ተቀብለው ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቀው እንግዶችን መቀበል እንደጀመሩ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ሆቴሎች በውጭ ለሚኖሩ 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አስተማማኝና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገዋል፡፡
ለኢትዮጵያውያኑ በሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች ላይ 25 በመቶ ቅናሽ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት፡፡
2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በቆይታቸው የኢትዮጵያን የተለያዩ ባሕሎች እና እሴቶችን ለማስተዋወቅ ሆቴሎች ልዩ ዝግጅት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡
በተለይም ባህላዊ የምግብ አይነቶችን፣ ባህላዊ አልባሳትን ፣ የብሔር ብሔረሰቦቸን ውዝዋዜ፣ የቡና አፈላል ሒደትን እና ሌሎች ባህላዊ እሴቶችን ለማሳየት ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡
ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 2ኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉባቸው የተለያዩ ሁነቶችን ለመዘጋጀት እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡
ሆቴሎች እንግዶችን ያለምንም የጸጥታ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ እና ሌሎች አገልግሎቶች ችግር ለማስተናገድ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቆ ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም ከፖሊስ ጀምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ወ/ሮ አስቴር አስረድተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ