የጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ጨቅላ ሕጻናት ሞት ቅነሳ ላይ ስኬትማ ሥራ መከናወኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የእናቶችን እና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ ባከናወነቻቸው በርካታ ሥራዎች ስኬት ማስመዝገቧን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ለአብነትም ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት በሕይወት ከሚወለዱ 100 ሺህ ጨቅላ ሕጻናት መካከል 1 ሺህ 250 ዎቹ ይሞቱ እንደነበር ያስታወሱት በሚኒስቴሩ የእናቶች፣ የሕጻናት፣ ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር መሠረት ዘላለም፤ ይህን አሃዝ በፈረንጆቹ 2020 ወደ 267 ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የሞት ምጣኔውን ዝቅ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የማሻሻያ መርሐ-ግብሮች፣ ፖሊሲዎች እና ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ ስኬቱ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
የማኅበረሰቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ-ግብር መስፋፋቱ፣ የእናቶች ጤና አገልግሎት ተደራሽነት ማደግና በገጠር የጤና አጠባበቅ መሠረተ ልማቶችን ማሻሻል ላይ ትኩረት መደረጉ ስኬቱ እንዲመዘገብ አስችሏል ብለዋል፡፡
የእናቶች እና ሕጻናት ጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል “የተቀናጀ የአጥቢያ ዙሪያ ሜንተርሽፕ”፣ የጤና ተቋም ወሊድን ለማጠናከር “የእናቶች ማቆያ ቤቶችን መገንባትና ማጠናከር” እንዲሁም በተለያዩ የክትባት ዘመቻ ሥራዎች ሌሎች አገልግሎቶችን አቀናጅቶ ማከናወን ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡
በአንጻሩ በመሠረተ-ልማት ሥራ ላይ የሴክተሮች ቅንጅት ማነስ፣ በግል እና በመንግሥት ተቋማት ያለው የቅንጅት እጥረት እንዲሁም የግል ጤና ተቋማት የመረጃ ልውውጥ ክፍተት መኖሩን እንደ ተግዳሮት አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የእናቶችን እና የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረገው ርብርብም÷ ወረርሽኝ፣ ግጭት፣ የዓየር ንብረት ለውጥ፣ የአንቡላንስ እጥረትና የአጠቃቀም ችግር፣ የሕክምና ቁሶችና መድኃኒቶች እጥረት፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሕክምናን የመጠቀም እውቀት ማነስ፣ የመለስተኛ የደም ባንክ በተፈለገው ልክ አለመስፋፋት መሰናክሎች ሆነዋል ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው