በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ነባርና አዲስ ተማሪዎችን እየጠሩ ነው
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲተዎች የነባርና አዲስ ተማሪዎችን የመመዝገቢያ ጊዜ እያሳወቁ ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀምሩ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም የባህር ዳር፣ ማርቆስ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲተዎች ነባር እና አዲስ ተማሪዎቻቸው የሚመዘጉበትን ጊዜ አስታውቀዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ1ኛ ዓመት ጀማሪ መርሐ ግብር 2ኛ ወሰነ ትምህርት ተማሪዎች እንዲሁም የ3ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ነባር መደበኛና የማታ ቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመግቢያ ጊዜ ከጥር 15 እስከ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ መሆኑን አሳውቋል፡፡
በ2016 ዓ.ም አዲስ የተመደቡ እና የማካካሻ መርሐ ግብር ተማሪዎች እንዲሁም በ2015 ዓ.ም የማካካሻ መርሐ ግብር ወስደው የማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ደግሞ ከጥር 21 እስከ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንዲመዘገቡ ዩኒቨርሲቲው ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተመሳሳይ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት 2ኛ ወሰነ ትምህርትና ከዚያ በላይ ነባር መደበኛ የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎች የመግቢያ ጊዜ ከጥር ከጥር 16 እስከ 17 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲሁም የ2ኛ ዓመት 2ኛ ወሰነ ትምህርት ነባር መደበኛ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ከጥር 23 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡
የ1ኛ ዓመት 2ኛ ወሰነ ትምህርት ነባር መደበኛ የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎች እና የ2016 ዓ.ም አዲስ ገቢ የ1ኛ ዓመት ተማሪዎችም ከየካቲት 7 እስከ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንዲመዘገቡ አስታውቋል፡፡
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲም የ2016 ዓ.ም ነባር መደበኛ ተማሪዎች የምዝገባ ጊዜ ጥር 2 እና ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡