በአማራ ክልል በ97 ቢሊየን ብር ወጪ 61 የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ነው
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ97 ቢሊየን ብር ወጪ 61 የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚሠሩ የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በባሕር ዳር ከተማ እየተገመገመ ነው።
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በአማራ ክልል በአጠቃላይ 61 የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶችን እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የመንገዶቹ አጠቃላይ ድምር ርዝማኔ 3 ሺህ 658 ኪሎ ሜትር ሲሆን÷ የመንገድ ግንባታዎቹ በ97 ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚገነቡ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ገልጿል።
በአዲስ ከሚሠሩ መንገዶች በተጨማሪ 3 ሺህ 664 ኪሎ ሜትር ነባር መንገዶች እየተጠገኑ መሆኑን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ከ2 ቢሊየን 166 ሚሊየን 529 ሺህ በላይ ብር ለመንገዶች ጥገና ተመድቦ እየተሠራ ስለመሆኑም ተነግሯል።
ውይይቱ በክልሉ የሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ወደ ጠንካራ አፈጻጸም ለማስገባት እና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን አቶ አረጋ ተናግረዋል።