Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ምርታማነትን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን ለማከናወን የግብርና ልማት ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ።

በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የግብርና ልማት አጋር አካላት ግንኙነት አማካሪ ምክር ቤት የመጀመሪያ ዙር የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ÷ የግብርና ሜካናይዜሽን አለመስፋፋትና የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስርዓቱ አለመጠናከር በክልሉ የግብርና ዘርፍ ላይ ተግዳሮት መሆኑን ገልፀዋል።

ዘርፉን ለማሳደግ አማካሪ ምክር ቤቱ ውጤታማ አጋርነት በመፍጠር ዘላቂነት ያለው የግብርና ልማት እንዲኖር አስተዋጽኦው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

በክልሉ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ በዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል በበኩላቸው÷ የግብርና መር ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግና ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን በማመንጨት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

ወጣቱ ያለውን አቅም ተጠቅሞ ወደ ግብርና እንዲገባና እንዲያለማ ለማድረግ ግንዛቤ መስጠትና መደገፍ እንደሚገባም መገለጹን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.