Fana: At a Speed of Life!

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ መሬት መረጃን የሚያዘምን ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት በተገኘ የ30 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ የከተማ መሬት መረጃን ለማዘመን የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ለዚሁ ፕሮጀክት ‘WAVUS JV’ ከተባለ ከሀገሪቱ መንግስት ኩባንያ ጋር የኮንትራት ስምምነት ተፈራርሟል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በፊርማ ስነ-ሥርዓቱ ወቅት ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ግንኙነታቸው የዳበረ ግንኙነት አላቸው ብለዋል፡፡
የሀገራቱ ግንኙነት በዲፕሎማሲው እና በልማት ላይ የተመሰረተ ብቻ ሳይሆን በደም የተሳሰረ በመሆኑ ስምምነቱ ይህንን ታሪካዊ ትስስር የበለጠ ያጠናክረዋል ሲሉም አክለዋል፡፡
በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ውስን የሆነውን የመሬት ሀብት በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት በመታገዝ ለዜጎች ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በአራት ከተሞች ተግባራዊ የሚደርገው ፕሮጀክቱ በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን እና የ’WAVUS JV’ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኪም ሀክ ሱንግ ተፈራርመዋል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሬትና የካዳስተር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙዓለም አድማሱ ፕሮጀክቱ በአዳማ፣ በሐዋሳ፣ በወላይታ ሶዶ እና በባህርዳር ከተሞች እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በድጅታላይዘሼን፣ በመሬት መረጃ አያያዝ ስርአት፣ በዳታ ማዕከል ግንባታ፣ በአቅም ግንባታ እና መሰል የዘርፉ ስራዎች ላይ እንደሚያተኩርም ማስገንዘባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.