Fana: At a Speed of Life!

የአ/አ ከተማ ከንቲባ የፕሮቶኮል ዳይሬክተርየነበሩትና የፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር የነበሩት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአ/አ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የፕሮቶኮል ዳይሬክተር የነበሩት እና የፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር የነበሩት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፖሊስን የጥርጣሬ መነሻ ምክንያትንና የተጠርጣሪዎችን የመከራከሪያ ነጥብን ተመልክቷል።

ተጠርጣሪዎቹ የአ/አ ከንቲባ የፕሮቶኮል ዳይሬክተር ኤልቤቴል ሀብቴ የነበሩት እና የፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር የነበሩት ፍቅሩ ኦላናን ጨምሮ አምስት ናቸው።

ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የጥርጣሬ መነሻውን ያቀረበው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ 1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪዎች ያላቸውን የስራ ኃላፊነት በመጠቀም የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ምንም ስራ የሌለውን የ1ኛ ተጠርጣሪ ወንድም ይስሀቅ ሀብቴ የተባለ ግለሰብ ትልቅ ባለኃብት እንደሆነና የተለያዩ እቃዎችን ከውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያመጣ የተለያዩ ግለሰቦችን እየጠቀመ እንደሆነ እና ከውጭ ሀገራት የሚያስመጣቸው እቃዎችን ደግሞ 1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪዎች በሚሰሩበት መስሪያ ቤት ባላቸው ስልጣን መሰረት ቁጥጥር እንደማይደረግና ከፍተኛ ትርፍ እንደሚያስገኝ በማስመሰል ተግባር ላይ ሚና እንደነበራቸው ጠቅሶ ፖሊስ በጥርጣሬ መነሻው ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።

3ኛ እና 4ኛ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ከግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን በተለያዩ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎችን በማግኘት ከ1ኛ ተጠርጣሪ ወንድም ጋር በጋራ እንደሚሰሩና ትርፋማ እንደሚሆኑ በመግለጽና በተለይም 1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪዎች በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ስልጣን ያላቸው መሆናቸውን በመግለጽ እንዲሁም እነዚሁ 1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪዎች እስከ ላይኛው የስልጣን ዕርከን ድረስ ሰንሰለት ያላቸው መሆናቸውን ጠቁመው፤ የግል ተበዳዮቹን ስጋት አይግባችሁ በማለት ነጋዴዎቹን ያግባቡ መሆኑን ጠቅሶ መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

በዚህ መልኩ ከ17 ግለሰቦች ዕቃ ማምጪያ በሚል 47 ሚሊየን 345 ሺህ ብር ከተቀበሉ በኋላ ከግል ተበዳዮች የሰበሰቡትን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ጠቅሶ መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ የጥርጣሬ መነሻውን ገልጿል።

በተጨማሪም የግል ተበዳዮቹ በሂደት የተፈጸመው የወንጀል ተግባር መሆኑን ተረድተው ገንዘባችንን መልሱ በሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ደግሞ 1ኛ፣ 2ኛ እና 5ኛ ተጠርጣሪዎች የ1ኛ ተጠርጣሪ ወንድም በህግ እንዳይጠየቅ ከአካባቢው ከሰወሩት በኋላ ወደ ግል ተበዳዮች ስልክ በመደወል በትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ስብሰባ እየጠሩ ”አርፋችሁ ተቀመጡ በዚህ ጉዳይ ሁለተኛ ስለገንዘብ እንዳታነሱ፣ የተለያዩ እንቅስቃሴ ብታደርጉና ወደ ህግ ብትሄዱ የምታመጡት ነገር የለም እንዲሁም በቤተሰባችሁና በራሳችሁ ላይ ጉዳት ይደርሳል በማለት የከፍተኛ ባለስልጣናትን ስም በመጥራት ሲያስፈራሯቸው ነበር ሲል የጥርጣሬ መነሻውን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

በዚህ መልኩ በከባድ ማታለልና ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ገልጿል።

የግል ተበዳዮችን ቃል መቀበሉንና የተወሰኑ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ ቀሪ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጾ፤ በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 59/1 መሰረት የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ምንም ወንጀል እንዳልፈጸሙ በመግለጽ ፖሊስ የጠየቀው የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮን በመቃወም ተከራክረዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የምርመራ መዝገቡ ጅምር መሆኑን ተከትሎ ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በማመን የ14 ቀን የምርመራ ማጠቃለያ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.