Fana: At a Speed of Life!

የ502 መስሪያ ቤት ኃላፊዎችን ስም የያዙ ማህተሞችን ጨምሮ የወንጀል ድርጊት ይፈጸምባቸው የነበሩ ቁሳቁሶች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ502 መስሪያ ቤት ኃላፊዎችም ስም ይዘው የተዘጋጁ ሀሰተኛ ማህተሞችን ጨምሮ የወንጀል ድርጊት ይፈጸምባቸው የነበሩ ቁሳቁሶች ተያዙ።

ፖሊስ በአራተኛ ሳምንት ኦፕሬሽን 728 መዝገቦችን ማደራጀቱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ በአዲስ አበባ ከተማ ለአራት ሳምንታት ባካሄዱት ኦፕሬሽን ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋለቸውን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በመግለጫቸውም÷ የፖሊስ ተቋማቱ ባለፉት ሶስት ሳምንታትያካሄዱትን የተቀናጀ ኦፕሬሽን ውጤት ግምገማ አቅርበዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በሶስተኛ ሳምንት ኦፕሬሽን በስራቸው በርካታ ተጠርጣሪዎችን የያዙ 28 መዝገቦችን አደራጅተናል ብለዋል በመግለጫቸው።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሞቱማ ሲና፥ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ የተለያዩ ሰነዶች አመሳስለው ሲያትሙ የነበሩ ቤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ቤቶቹ በውስጣቸው 502 የመስሪያ ቤት ኃላፊዎች ማህተም፣ 26 ጥቅል ዕፅ፣ 85 ሺሻ ቤቶች እንዲሁም 925 የቁማር መጫወቻ ቁሳቁሶች ተይዘዋል ብለዋል።

ከውንብድና ወንጀል ጋር በተያያዘ ሹፌሮችን በመግደል የተዘረፉ 2 ተሽከርካሪዎችን ተከታትሎ በመያዝ ለባለቤቶቹ መመለስ ተችሏል ብለዋል።

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ያሲን ሁሴን፥ የግለሰቦችን ቤት ተከራይተው 130 ሲም ካርድ በመያዝ ከባንክ ጋር ባላቸው ግንኙነት ወደ ተለያዩ ሥልኮች እየደወሉ የማጭበርበር ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በክፍለ ከተማው 3 ሺህ 794 ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር፣ ከ162 ሺህ በላይ ብር እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ተይዘዋል ብለዋል።

በተለይም የበዓል ሰሞን እንደመሆኑ መሰል ወንጀሎች የመፈፀም እድላቸው ሰፊ ነው ያሉት ኮማንደሩ፥ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

የላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ሽመልስ ሽፈራው በበኩላቸው፥ በርካታ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን ገልፀዋል።

በዚህም 10 ሽጉጦች፣ 39 ታብሌት እና ኮምፒውተሮች፣ 1 ሺህ 835 የመኪና ዕቃዎች፣ 949 ሞባይሎች እና 45 ቴሌቪዥኖች መያዛቸውን አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ በክፍለ ከተማው የወንጀል ድርጊት 50 በመቶ መቀነሱንም አንስተዋል፡፡

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.