የሀገር ውስጥ ዜና

በሕገ-ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች እንዲመዘገቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

By Alemayehu Geremew

January 10, 2024

በሕገ-ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች እንዲመዘገቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጪ ሀገር ዜጎች ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንዲመዘገቡ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አሳሰበ።

የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ማስተዋል ገዳ÷ ምዝገባው ቪዛ እና የመኖሪያ ፈቃዳቸው አገልግሎቱ ያለፈ እንዲሁም የድርጅት ምዝገባ ሳያደርጉ ተቀጥረው የሚሠሩትን የውጭ ሀገር ዜጎች እንደሚመለከት ገልጸዋል።

ምዝገባው የሚካሄደው በአገልግሎቱ ዋና መስሪያ ቤት ሲሆን በመንግሥት የሥራ ሠዓት ሠነዶቻቸውን በመያዝ መጥተው ሕጋዊ ማድረግ አለባቸው ተብሏል፡፡

አገልግሎቱ ባደረገው ማጣራት ከ21 ሺህ የሚበልጡ የውጭ ሀገር ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚኖሩ ማወቅ ተችሏል።

ሐሰተኛ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ የያዙ÷ ከ18 ሺህ በላይ፣ ሐሰተኛ ቪዛ የያዙ ከ 1 ሺህ 500 በላይ እንዲሁም ከ1 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑ ደግሞ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን መታወቂያ የያዙ መሆናቸው በተደረገ ማጣራት ለማወቅ መቻሉ ተመልክቷል፡፡

ማሳሰቢያው የሚመለከተው ሥደተኛ ሆነው የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ሳይሆን ሐሰተኛ ሠነድ ይዘው የሚንቀሳቀሱትን ነው ተብሏል፡፡

በመሳፍንት እያዩ