የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ስምምነት በጋራ የመልማት ቀጣናዊ ፖሊሲን እንደሚያጸና ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅና በቀጣናው የምትከተለውን በጋራ የመልማት ፖሊሲ የሚያጸና መሆኑን ሚኒስትሮች ገለጹ።
የባህር በር የማግኘት ጉዳይ የህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ በአንድነት ሊቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ የመልማትና የጋራ ብልፅግናን የማረጋገጥ ፖሊሲን እየተገበረች መሆኗን ገልጸዋል።
ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ እያደገ ያለውንና ለጎረቤቶቿ የሚተርፈውን ኢኮኖሚዋን ታሳቢ ያደረገ አማራጭ ወደብንና የባህር በርን የሚያስገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቀጣናው ሀገራት በህዝብ፣ በባህል፣ በመልክዓምድር፣ በታሪክ የተሳሰሩ መሆናቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ውህደትን ለማምጣት ለያዘችው አቋም የባህር በሩ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር፣ ኢ/ር) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የባህር በር በማጣቷ ለብዙ ችግሮች ተዳርጋ ቆይታለች ብለዋል።
የባህር በር አልባ መሆኗ እንደ ሀገር ኢኮኖሚያዊና ጂኦፖለቲካዊ ጫና ማሳደሩን ጠቅሰው÷ ጫናው በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ የሚያርፍ ስለመሆኑ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ሰፊ የህዝብ ቁጥር እና በፍጥነት እያደገ ያለ ብዝሃ የኢኮኖሚ ስርዓት ያላት በመሆኑ ይህንን የሚሸከም አማራጭ ወደብ አለመኖሩም ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም የሚጨምርና ለቀጣዩ ትውልድ ኩራትን የሚያወርስ ታሪካዊ ስምምነት ስለመሆኑም መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡