Fana: At a Speed of Life!

የባሕር ኃይሉ በአሠራርና አደረጃጀት አቅሙን እያጠናከረ መምጣቱ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕር ኃይል በአሠራርና አደረጃጀት አቅሙን በይበልጥ እያጠናከረ መምጣቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነት እና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል።

ቋሚ ኮሚቴው በባሕር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተገኝቶ ጉብኝት ካደረገ በኋላ ተቋሙ እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራት ዙሪያም ውይይት ተካሂዷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ መሃዲ (ዶ/ር)÷ ባሕር ኃይሉ ከለውጥ ወዲህ በአዋጅ እንደገና ከተቋቋመ ጀምሮ እየተጠናከረ መምጣቱንና በከፍተኛ ዕውቀትና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየተመራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህ አቅም መንግስት የተፈራረመውን የባሕር በር ስምምነት ወደፊት ለማራመድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው÷ ቋሚ ኮሚቴውም ባሕር ኃይሉን እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል፡፡

የባሕር ኃይል ምክትል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ናስር አባዲጋ÷ ባሕር ኃይሉ በሰው ኃይል፣ በስልጠና፣ በልምድ ልውውጥ እንዲሁም ተቋሙን ከማደራጀት አንፃር በርካታ ሥራዎችን ሲያከናወኑ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ ራሱን ለማደራጀት በሚያደርገው ጥረትም ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር ዴዔታ ማርታ ሊዊጂ በበኩላቸው÷ የፈረሰውን የባሕር ኃይል በአዋጅ አቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉ ሀገሪቱ በስትራቴጂ፣ በፖሊሲ እና በዕቅድ እየተመራች መሆኗን ማሳያ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ባሕር ኃይሉ በሰው ኃይል ጭምር በአግባቡ መደራጀቱንና የባሕር በሩ ሥራ ሲጀምር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ፀጥታና ደኅንነትን የሚያስጠብቅ እንዲሁም የመረጃ አቅምን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.