የወንጪ ፕሮጀክት
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገበታ ለሀገር አንዱ አካል የሆነው የወንጪ ፕሮጀክት መጋቢት 11 ቀን 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በወንጪ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን÷ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ከአዲስ አበባ በ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ወንጪ 3 ሺህ 380 ሜትር ከፍታ ላይ ሲገኝ ሃይቅና ፍል ውሃን ጨምሮ እጅግ ማራኪ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶችን ይዟል።
በአካባቢው የሚገኘው ደንና በውስጡ ያሉት ብርቅዬ አዕዋፋት ዝማሬ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ተጀምረው እውን እየተደረጉ ካሉ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የወንጪ ፕሮጀክት አስተባባሪ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም እንደተናገሩት÷ ስራው በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚካሄድ ነው።
በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ ወንጪ ሃይቅ የሚወስደው የአስፋልት መንገድ፣ ሁለቱን ሃይቆች የሚያገናኝ የአስፋልት መንገድ፣ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት፣ የጤና ማዕከል፣ ትምህርት ቤቶች፣ የቴሌኮም ማሻሻያ ፕሮጀክት እንዲሁም በባለሃብቶች የሚገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ ማዕከሎችን የሚያካትት እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም፣ የጤና ማዕከል፣ የቴሌኮም ማሻሻያ፣ በግል ባለሀብቶች የሚሰሩ መዝናኛ ስፍራዎች እንዲሁም የትምህርት ማዕከል እና አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ይገነባል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ቱሪስቶችን በስፋት የመሳብ አቅም እንዳለው የሚነገርለት የወንጪ ፕሮጀክት የአካባቢው ነዋሪዎችም በብዙ እንደሚጠቀሙ ታምኖበታል፡፡