ርዕሰ መስተዳድር አረጋ የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ አያያዝ ሥራዎችን በጥንቃቄ አከናውኗል አሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ አያያዝ ሥራዎችን በከፍተኛ ጥንቃቄ ማከናወኑን ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ጋር ባደረጉት ውይይት÷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ተጠርጥረው የተያዙ ዜጎች የሰብዓዊ አያያዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የቦርዱ ሠብሣቢ አዝመራ አንዴሞ የክልሉ የሰላም ሁኔታ እየተረጋጋ መሆኑን ተመልክተናል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የመርማሪ ቦርዱ ሥራ በዜጎች ላይ አላስፈላጊ የሰብዓዊ ጥሰት እንዳይኖር መከታተል መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ምልከታ በተካሄደበት አካባቢ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ገልጸው÷ ተጠርጣሪዎች የተሀድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ማሕበረሰቡ መመለሳቸው በበጎ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡
ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች በቂም በቀል የሚታሰሩ ወገኖች አሉ የሚል ጥያቄ መነሳቱን ጠቅሰው÷ መንግሥት ከሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመርመር እና ማስተካከል እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡
በተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገው ምርመራ መፍጠን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ነጃት ግርማ (ዶ/ር)÷ በተደረጉ ውይይቶች ሕዝቡ ሰላም ፈላጊ መሆኑን፣ ከግጭቱ መማሩን እና ለጥያቄዎቹም መልስ እንደሚፈልግ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ በበኩላቸው÷ በግጭት ውስጥ የነበሩ ኃይሎች አሰላለፍ ልየታ መደረጉን አንስተዋል።
የክልሉ ችግር የተፈጠረው በዋናነት ለዘመናት በተነገረው የሐሰት ትርክት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመንግሥት መዋቅር እስከታችኛው ድረስ እየተዘረጋ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ አሁን ላይ በተወሰደው እርምጃ ከፊት ለፊት ውጊያ ወደ ሽምቅ፣ ከሽምቅ ወደ ሽብር ተግባር መውረዱንም አስረድተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ አያያዝ ላይ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሠርቷል፤ ከሰብዓዊ አያያዝ ጋር ስህተቶች ካሉም እየተከታተልን እናስተካክላለን ነው ያሉት።
በግጭቱ እየነገዱ ያሉ ኃይሎች ግጭት በመፍጠር ገቢ ለማግኘት ሙከራ እያደረጉ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ከሕዝብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ውይይት ያደረገው ክልሉ፤ አሁንም ለውይይት በሩ ክፍት እንደሆነ አረጋግጠዋል።
የተደረገው የሰላም ጥሪ በሕገ መንግሥቱ ይቅርታ ከማይደረግላቸው ወንጀሎች ውጭ ከዚህ ቀደም የነበሩ ወንጀሎችን ይቅርታ እንደሚያሰጥም አመላክተዋል፡፡
የቀረበውን የሰላም ጥሪ የተዛባ ትርጉም በመስጠት የሚናፈሰው ወሬ ትክክል እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግሥት በሰላም ለሚገቡ ኃይሎች ትጥቃቸውን ሕጋዊ እያደረገ እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ህጋዊ መንገድን መከተል እንደሚገባ ገልጸው፤ ከየትኛውም አካል ጋር ለመወያየት እና ችግሮችን በሰላም ለመፍታት መንግሥት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሰላም የሚገቡ ኃይሎች ቁጥር ከቀን ቀን እየጨመረ ነው፤ ይህም ለክልሉ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!