Fana: At a Speed of Life!

በዘላቂነት የግንባታ ግብዓት ገበያውን ለማረጋጋት የአምራቹን ዘርፍ ማበረታታት እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮንስትራክሽን ግብዓቶች አንፃራዊ የገበያ መረጋጋትን ዘላቂ ለማድረግ የኃይል አቅርቦት ችግርን መፍታት እና የሀገር ውስጥ አምራቹን ዘርፍ ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ተመላከተ፡፡
 
የኮንስትራክሽን ዋና ዋና ግብዓት ገበያ አንፃራዊ ለውጥና መረጋጋት ማሳየቱን በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ተቋራጮች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረትና የመተካት ጥረት አነስተኛ መሆን ብሎም በሌሎች ድምር ውጤቶች የዘርፉ ዕድገት ተፈትኖ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡
 
አሁን ላይ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋቱ፣ ያለ ሦስተኛ ወገን አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ግብዓት ተጠቃሚዎች በቀጥታ የሚገናኙበት ሁኔታ በመመቻቸቱ የዘርፉ ገበያ መረጋጋት አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
 
በአንፃራዊነት የታየውን አሁናዊ የግንባታ ግብዓት ገበያ መረጋጋት ዘላቂ ለማድረግም÷ ከኢንዱስትሪው ማደግ፣ ከሕዝብ ቁጥር መጨመርና ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የኃይል አቅርቦት ችግርን መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡
 
በተጨማሪም በቴክኖሎጂ የታገዙና ሥነ-ምኅዳርን ማዕከል ያደረጉ ግንባታዎችን ማከናወን እንዲሁም የሀገር ውስጥ የማምረቻውን ዘርፍ ማበረታት እና የአልሚዎችን ቁጥር ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
 
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታምራት ሙሉ (ኢ/ር) በበኩላቸው፥ የኃይል አቅርቦት ችግሩን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማምረት ሲችል እንደሚፈታ አስታውቀዋል፡፡
 
በቂ የኃይል አቅርቦቱ ሲኖር ደግሞ ነባር እና አዳዲሶቹ የማምረቻው ዘርፍ ኢንዱስትሪዎች በአቅማቸው ልክ ማምረት ሲጀምሩ ተግዳሮቶቹ በዘላቂነት ይፈታሉ ብለዋል።
 
ኢንዱስትሪው የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ከማምጣት፣ ከማለማመድና ብቁ ባለሙያዎችን ከማፍራት ጎን ለጎን፥ አዋጭ የግንባታ ግብዓቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ እንዲቋቋሙ የማበረታታት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት፡፡
 
በኮንስትራክሽን ዘርፉ 80 በመቶ የሚሆነውን ዋና ዋና ግብዓት በአጭር ጊዜ በሀገር ውስጥ ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡
 
በመራኦል ከድር
 
 
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.