የወንጀል ድርጊቶችን ካሉበት ሆነው ለፖሊስ የሚያደርሱበት መተግበሪያ ሥራ ሊጀምር ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወንጀል ድርጊቶችን ዜጎች ካሉበት ሆነው ለፖሊስ የሚያደርሱበት የሞባይል መተግበሪያ በቅርቡ በአዲስ አበባ ሥራ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አስታወቁ፡፡
ፌዴራል ፖሊስ ከለውጡ በኋላ የሀገርንና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ አቅሙን በማሳደግ የሕዝብና መንግሥትን ኃላፊነት በላቀ ብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቴክኖሎጂ በመታገዝ እንዲሁም ከኅብረተሰቡ ጋር በሚያከናውናቸው የጸጥታና ደኅንነት ሥራዎች የሰላም ማስጠበቅ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የሰው ኃይል አቅሙን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በአፍሪካ እስካሁን ያልተሞከረ በዓለም ላይም እምብዛም ያልተለመደ የዜጎችን የጸጥታ ሥራ የሚያግዝ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የበለፀገ ዘመናዊ የሞባይል መተግበሪያ ሥራ ላይ ይውላል ነው ያሉት፡፡
መተግበሪያው ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው የወንጀል ድርጊቶችን ለፖሊስ ማድረስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቁመው÷ በቅርቡ በአዲስ አበባ ሥራ እንደሚጀምር አመላክተዋል፡፡
መተግበሪያው ዜጎች በእጅ ስልካቸው ለፖሊስ መረጃ የሚያደርሱበትና በወንጀል መከላከል ሥራ የፖሊስና ሕብረተሰቡን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገልፀዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!